Friday, June 29, 2012

ለመሆኑ አንድነት ማለት ምን ማለት ነው?

                                                                                                                          ገለታው ዘለቀ
                                                                                   
 መቼስ ትውልዶች የየራሳቸውን አስተዳደራዊ ዘዪ እያበጁ መኖር ፖለቲካዊ ወግ ነው;; የአስተዳደር ሂደት ዳይናሚክ ወይም ቀኖና በመሆኑ በየጊዜው ቢለዋወጥ ተፈጥሮአዊነት አለው;; ታዲያ በዚህ የለውጥ ሂደት ወቅት የማያልፈው ሃገር ነው;; የሃገር ሉኣላዊነት እና አንድነት ጉዳይ የትውልዶች ሁሉ ዶግማዊ ኪዳን ነው;;  ይህች አገር የኛ ትውልድ ብቻ አይደለችም::ያለፈው  የአሁኑ  እና ገና በአብራካችን ያሉ እልፍ ትውልዶች ሁሉ ናት::አሁን በህይወት ያለው ትውልድ ሊመጣ ካለው  እና ካለፈው ትውልድ ጋር ሲነጻጸር እንደ ኢምንት ነው::ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ የማያልፈው  ሃገር ነው;;ይህ በህይወት ያለው ትውልድ አጭር  ዘመኑን  ኖሮ ልክ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ለሚመጣው  አቀብሎ የማለፍ ግዙፍ ሃላፊነት ትከሻው ላይ አለ ;;
   መንደርደር ሳናበዛ ወደ ዋናው የመወያያ ሃሳብ እንውረድ;;ለመነሻም  አንድነት ለመሆኑ ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ሃገራችን አንድ ናት እኛም ህዝቦቿ አንድ ነን ስንል ምን ማለታችን ነው? ሃገራችን ኢትዮጵያ የተለያዪ ቋንቋ እና ባህል ያላት ሆና እያየን አንድ ናት ስንል ይህንን ልዪነት መካዳችን ነውን? በአንድ ፖለቲካዊ መዋቅር ስር መሰንበታችን ብቻ ነው የአንድነታችን መቋጠሪያው? እንዲህ ተለዋዋጭ በሆነው ፖለቲካ ላይ የተሰራች አገር ናትወይ  ኢትዮጵያ? እነዚህን ጥያቄዎች ለራሳችን ስንመልስ እና የጠራ ግንዛቤ ሲኖረን በርግጥም የትግላችንን የታችኛውን መሰረት በሚገባ አበጀን ግልብ ስሜት ነጻ ሆነንም ሃገራችንን ለመታደግ ሳንታክት እንሰራለን ብዪ አምናለሁ;;በመርህ ላይ የተመሰረተ መረዳት ስናዳብር ቦግ እልም የሚል ትግል አይኖርም;;በስድብ ሃይላችንንም አንጨርስም;;ጠብቀን እንድንታገል የሚያደርገንን ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ታጥቀናልና;; ታዲያ እንግዲህ ከፍ ሲል ያነሳናቸውን መሰረታዊ መነሻዎች አውራጅ አርጌ የገባችኝን ሃሳብ ለወገኖቼ ለማቀበል ነበር አነሳሴ;;ዝቅ ሲል የምናያችው አራት ኢለመንቶች የኢትዮጵያ ዋልታና ማገሮች የኛ ዜጎቹ ደግሞ የጋራ መልካችን አርጌ ወስጄአለሁ;;እስቲ ዝቅ ሲል ያዝ ለቀቅ እያረግን ለማየት የገባንን ያህል የኢትዮጵያን ስሪት እንደሚከተለው ለውይይት ያህል እናንሳ ;;
            

           የአንድነታችን መሰረቶች
     

1) ታሪክ
2) ማህበራዊ ካፒታል
3) መሬት
4) አስተዳደር እና ፍትህ

ከታሪክ እንነሳ
    ታሪክ የሞተ ነገር አይደለም;; ታሪክ ሰሪዎች ናቸው ያለፉት;;ታሪክ ሁል ጊዜም ህያው ነው;;ዛሬ ደግሞ የትላንትና ውጤት ነው;; ኢትጵያ ሃገራችን ባለ ብዙ ታሪክ ናት;; ክፉና ደጉን ሁሉ አልፋ ዛሬ በእኛ እጅ ትገኛለች;;ከምንኮራባቸው ታሪኮቻችን መካከል በቅኝ ግዛት አለመገዛታችን እና አለመግዛታችን የራሳችን ፊደል ያለን መሆናችን ይህም በዚያን ዎቅት አባቶቻችን የነበራቸውን በራስ መተማመን እና በወቅቱ ስልጣኔ ተፎካካሪ እንደነበርን ያሳያል;;በዴሞክራሲው ስርኣት ግንባታ ደግሞ የገዳ ስርአታችን ለአለም ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማስተማር ይበቃል;; አድዋ ድላችን የማይጨው ተጋድሎአችን የኛ የኢትዮጵያውያን ሃብቶች ናቸው ;;ሁላችን ኢትዮጵያውያን ይህንን ታሪክ ስንጋራ አንድነታችን በዚህም ይገለጻል;;ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንልም አንዱ በውስጥ ያለው ኢለመንት የጋራው ታሪካችን ነው;;ለሃገር አንድነት ዋናው መሰረት ታሪክ ነውና መንግስታት ታሪክን ማጉደፍ አይችሉም;;ይህ ማለት ካለፈው ስህተት አንማር ማለት አይደለም;;ነገር ግን የአንድነት መሰርት የሆነንን ታሪክ እንደ የጋራ ሃብትነቱ መጠ በቅ መንከባከብ የመንግስታት ዋና ተግባር ነው;;
    አሳዛኙ ነገር ታዲያ ይህ መንግስት ስለምን ነው ታሪክ የሚያንኳስሰው? ታሪክንስ ማከፋፈል ለምን አስፈለገው? የሚለውን ስንጠይቅ ነው;; አክሱም ሃውልት ወላይታውም ኢትዮጵያዊ ካልሆነ የአንድነታችን  ወዙ የት ጋር ነው? ታሪክን ማከፋፈል ማለት በትክክል አንድነትን ለመናድ የሚደረግ የመጀመሪያ ደረጃ አፍራሽ ተግባር ነው;;በታሪካችን የተገኙትን ጉድፎች እየነቀሱ እያዎጡ ለአንድ ወገን የማሸከም አዝማሚያም ይታያል;;ይህም ጥላቻን በመሳብ አንድነትን ለማፍረስ የተደረገ ነው;;ክፉን ደጉን ታሪካችንን ስንጋራ እና  ቁሳዊ ታሪካችንን ስንጋራ አንድነታችን ያብባል;;አንድ ነን አንድ ህዝብ ነን ስንልም አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ይሄው ክፉና ደጉን ታሪካችንን መጋራታችን የሰጠን መልክ ነው;;


ሁለተኛው የአንድነታችን ኢለመንት ማህበራዊ ካፒታል ነው;;

በዚህ አገባብ ማህበራዊ ካፒታል ማለት በአራቱም ማዕዘናት ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚተሳሰሩበት ምግባር ወይም ድር ነው;;ይህ ድር በተለይ በስነ-ልቦና  እንድንገናኝ እና እንድንተማመን በሃገራችን አቋራጭም ይህ የመተማመን ስሜት ካንዱ ወደ አንዱ ያለማቋረጥ እንዲፈስ የሚያደርግ ምግባር ነው ;;  በዚህ ድር አማካኝነት ርስ በርስ ንክኪ(interaction) ጊዜ ባህርይ እየተጋባን ወደ ፍጹሙ የጋራው እሴት እያደግን የምንሄድበት የውህደት ጎዳናችን ማህበራዊ ሃብታችን ነው ;; ቀላል እና ተግባራዊ ጉዳዮችን እናንሳ;;ለምሳሌ ;- ሃገራችን የተለያዬ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ህዝቦች በተለይም ጂኦግራፊ የተጎራበቱ እሴቶችን ሲያዋህዱ ይታያሉ ይህ ሂደት የስነ ልቦና መቀራረብን ብሎም እና መተማመንን እንዲሁም መከባበርን ጠንካራ የአንድነት ስሜትን ያመጣል;;
 ሁሉን ኢትዮጵያ ቋንቋ መናገር ባልችልም ብዙ ቋንቋዎች ግን አሉኝ;;የተለያዪ አለባብስ ባለቤትም ነኝ;;ለእኔ ቋንቋ ልዩነትም ሆነ የባህል ልዩነቶቻችን ጌጦቼ እንጂ የወሰን መከለያ ድንጋዮች አይደሉም;;ወደሚል ከፍታ ስንደርስ እና በዚህ ስሜት ስን ገናኝ አንድነታችን በዚህም ይገለጻል ማለት ነው;;ይህ ድር ሲበጠስ አንድነታችን እየተናጋ ይሄዳል;;ማህበራዊ ካፒታላችን ዶግማ ነው;;የፈለገው ፖለቲከኛ ይህንን የጋራ እሴት ድር  ሊቆርጥ አይገባውም;;ይሄ መንግስት ከሚያጠፋቸው ጥፋቶች ሁሉ የላቀው ይህንን ካፒታል ለማበላሸት ተግቶ መስራቱ ነው;;ይህ ድር ልማት ሃገርን ላማሳድግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን አንጻሩ ድሩን የሚያዎሳስብ ወይም የሚቆርጥ እንቅስቃሴ ሁሉ ጸረ ኢትዮጵያነት ጸረ አንድነት ነው;;  
ይህ መንግስት ኢትዮጵያ በሰፈር በቋንቋ የሚሰፍሩባት እንድትሆን ሲያደርግ ይህንን እያደገ የመጣውን ማህብራዊ ካፒታል የማሳጠር ብሎም ውህደትን የማጓተት ዘላቂ ግብ ይዞ ይመስላል;;ይህ ደግሞ ልዪነትን እያሰፋ አንድነትን እያኮሰሰ የሚሄድ ተግባር በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ጠብቀው ሊታገሉት ይገባል;እንደው በሰፈራችን የተገኘውን ታሪካዊ ቅርሳቅርስ ይዘን ከዚህ ወዲያ የኔ ነው ሌላው ወገን አያገባውም ማለት ከደከመ ስነ-ልቦና የሚመነጭ አስተሳሰብ ይመስላል;; በብዙ ህብር ያጌጠችው ኢትዮጵያ አራቱም ማእዘን ያላትን ባህል ቋንቋ ወግ ልማድ ሁሉ ለጋራው ውብ እሴት ግንባታ መስዋእት እያደረገች በውህደት ጎዳና ላይ ናት;; ይህ የጋራው እሴት ፍጹሙ መልካችን ሲሆን በከፍተኛ መዋጮ የተሰራ በመሆኑ ውበቱ ሌላ ነው;;ይህንን ጉዞ ለማዘግየት ወይም ለማጥፋት የሚደረግ ሴራ የከፋ በደል በመሆኑ ዜጎች ሽንጣቸውን ገትረው ሊቋቋሙት ይገባል;;



ሌላው የሃገር ኢለመንት መሬት ነው;;
በመሬት እና መካከል ያለው መስተጋብር የየ ሆድ እና የየ መጠለያ ጣጣ ብቻ አይደለም;;ከዚህ ገዝፎ በሄደ የተፈጥሮ  መብት ጋርም ይያያዛል;;ወደዚህች ምድር ስንመጣ እጣ ክፍላችን ገመዳችን የወደቀባት ሆና የተገኘችው ኢትዮጵያ ናት;; አገራችን ሰፈራችን ሳይሆን ኢትዮጵያ ናት;; ሰላሌ የተወለደው ኢትዮጵያዊ  ሰላሌያዊ ሊባል አይችልም ኢትዮጵያዊ እንጂ;;ለኔ ጎጃም ሄዶ ጎጆ የመቀለስ መብቴ እና አሩሲ ጎጆ ቀልሶ የመኖር መብቴ በግል ምርጫዪ የተመሰረተ እንጂ ከሰፈሬ ስወጣ የውጭ ሃገር ያህል እንዲሰማኝ የሚያድርግ ድባብ ሊፈጠር አይገባውም;;ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግልም ይሁን በቡድን በአራቱም የኢትዮጵያ ማእዘናት በፈለጉት ያየር ጸባይ የመኖር መብታቸው እኩል እኩል ሲሆን  አንድነታችን በዚህም ይገለጻል;;ይህ አንድነት በጦርነት ጊዜ በልማት ጊዜ የሚገለጥ ነው;; ጦርነት ሲፈጠር አንድነትን እየሰበኩ ለልማት ጊዜ እግዜር ይስጥልኝ ብሎ ማሰናበት የሚዛን መዋዥቅ ነው;;
  ከፍ ሲል እንዳልነው ከሃገራችን ጋር ያለን ፍቅር ከሆድ በላይ ነው;;ስጋዊ ግንኙነታችን በሆነ አጋጣሚ ቢቋረጥም ሃገራዊ ፍቅራችን ግን እያበበ ይሄዳል;;ለዚህም ነው በየ ሃገሩ ተዘልሎ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የተዘለለባትን ምድር ፍሬ እየበላ ከሃገሩ መሬት ጋር ያለው ሆዳዊ ግንኙነት ቢቋረጥም ግን ያገሩ ነገር ያንገበግበዋል;;ኢትዮጵያ እጣ ክፍሉ ናትና;;እንግዲህ የመሬት አንድነት ስንል ሁሉ ኢትዮጵያዊ በፈለገው ኢትዮጵያ ግዛት ለመኖር ሲመርጥ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሳይሰማው ሲቀርና ሁሉም የሃገሩ ክፍል የኔ ነው የሚል መተማመን ሲያዳብር እንዲሁም ደሞ በረገጥነው መሬት እኩል እኩል የመሬት ህግ ስንዳኝ  እኩልነታችን በዚህም ይገለጻል;;
   ይህ አንድነታችን መሰረት በብዙ ተናግቷል;; የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በቋንቋ በቋንቋ በጎሳ በጎሳ ተበል ዋና ዋና የአንድነቶቿ መሰረቶች ተናግተው በዎታደር ተጠርንፋ የምትኖር ትመስላለች;; ከዚህ አልፎ ብሄሮች ሰፈራቸውን ይዘው መገንጥል ዲሞክራሲ ነውም ተብሏል ;; ህጉ ባልና ሚስት ለማፋታት የሚጨንቀውን ያህል ያገር መገንጠል ጉዳይ የማያስጨንቀው ይመስላል;;እንዲህ አንድ ትውልድ ኢትዮጵያን የመገንጠል ስልጣን እንዴት ሊኖረው እንደሚችል አይገባኝም;;ያውም ሌላው የኢትዮጵያ ልጅ ሳያገባው አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ መወሰን ይችላሉ;;በመሰረቱ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የመገነጣጠል ውሳኔ ለማሳለፍ የሚከተሉት ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች  መታሰብ አለባቸው;;እነዚህም;;-
     1) ለዚህች አገር መቆም የሞቱ ኢትዮጵያውያን በትንሳኤው ሃይል ተነስተው ድምጻቸውን ሊሰጡ ይገባል;;
     2)አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ በሰፈሩ ሳይሆን እንዳገር ድምጹን ሊሰጥ ይችላል
      3) አብራካችን ያሉ እልፍ ትውልዶች ገና አገራችው ልትሆን ነው እና በጣም ይመለከታቸዋል;; በሆነ ኪነ ጥበብ ይምጡና ድምጻቸውን ያሰሙ;;ባለፈው ይህንን ሃሳብ ለመጻፍ ልቤ ሲነሳ እነዚህን ሶስት ጉዳዮች ላንድ ጓደኛዪ ባጫውተው ፈገግ አለ;; የማይሆን ነገር ለማዎዳደር ሞከርክ ለማለት እንደሆነ ስሜቱ ያሳብቃል;;ለማሳየት የፈለኩት የዚህን ትውልድ የሃላፊነት የሸክም ክብደት ነበር;;
ለዚህ ነው አገር በፖለቲካ ሂደት ዎቅት ዶግማ ነው የምንለው;;የመጣ ትውልድ ቢስማማ ሊጠብቃት ባይስማማ ሊያፈራርሳት የሚችላት ሸክላ ቢጤ አይደለችም አገር;;ጨዋ ትውልድ በህይውት ዘመኑ የራሱን አስተዳደር ዘርግቶ ከምድሪቱ ፍሬ ሲበላና ሲጠጣ ሰንብቶ የዘመኑ መቋጫ ሲደርስ ለተተኪው አስረክቦ ማለፍ ነው ያለበት;;በዚህ የማያቋርጥ ሂደት ዎቅት የሃላፊነት ስሜት ያየለባቸው ትውልዶች ትርፍ ልማት ያለሙ ያለፈውን ትውልድ አክብረው ለሚመጣው ደግሞ ቅርስ ትተው ይነጉዳሉ;;

ሌላው ኢለመንት አስተዳደር እና ፍትህ ነው;;

  አስተዳደሩ እና ፍትሁ በዘር እና በብሄር ከተቃኘ ያለ ጥርጥር እኩልነት አይኖርም;;እኩልነት ማጣታችን ደግሞ ዞሮዞሮ አንድነታችንን ያኮስሳል;;አንዱ አንድ ነን የሚያሰኘን መልካችን በፍትህ ፊት እኩል ቁመት አንድ አይነት መልክ ሲኖረን ነው;;በዚህ በኩል ያለው ኢትዮጵያ አንድነት ዘዎትር እንዳነከሰ ነው;;እውነተኛይቱ ፍትህ ዘር ብሄር ስልጣን የሚያይ አይን የላትም;;ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንድ ናቸው;;ጓደኛዪ በዘሩ ምክንያት ከኔ የተሻለ ጥቅም ሲያገኝ ባዝን ብቆጣ ቀንቼ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ዕኩልነቴ ስለተደፈረ ነው;; እሱ በፍትህ ፊት ረዝሞ ከታየ አሁን አንድነታችን ያለ ጥርጥር ተናግቷል ማለት ነው;;በፍትህ ፊት ቀጥሎ ተሰላፊ የለም;;
    ኢትዮጵያዊያን አንድነትን ከሚፈልጉበት አውድ መካከል አንዱ በፍትህ ፊት በዕኩል እኩል መታየት ነው;;በእኩልነት የመዳኘት ከባቢው ሲሰበር ዜግነት ትርጉም ያጣል እኩልነት ሲቀርም አንድነት ያዘማል;;የፍትህ ደጅ  አንድነታችንን የምንፈትሽበት አውድ ነው;;ዜጎች በፍትህ መአዛ ሳይሳቡ ሲቀሩ ከባድ ተስፋ መቁረጥ ይሆናል;; ዛሬ ኢትዮጵያ ሁለት ህግ የምትተዳደር ይመስላል;;አንደኛው ያልተጻፈው ህግ ሲሆን ይህም የመሪዎቹ ፍላጎት ነው ሌላው ክስት ብሎ የሚታየው ደሞ የተጻፈው ነው;; ያልተጻፈው የመሪዎች ፈቃድ በከፍተኛ ደረጃ በተጻፈው ላይ የበላይነት አለው;;የባለስልጣናቱ ቁጣ ከነደደ የተጻፈው ህግ ይሽቆጠቆጣል;;ያልተጻፈው ህግ ፍላጎቱን ለመሙላት ሲሻ አንዳንዴ ይህን የተጻፈውን ይጠቅሰዋል እማይገናኘውን እንዲያገናኝ ተደርጎ የተጻፈው እንዲፈርድ ይደረጋል;;ዜጎች በተጻፈው ይከሰሱና ባልተጻፈው ይቀጣሉ አንዳንዴ ደሞ ባልተጻፈው ይከሰሱና በተጻፈው ህግ ይፈረድባቸዋል;;በዚህም ምክንያት ሃብት ዘር ስልጣን በህግ ፊት የተለያየ መልክ ሰጥተውናል;; ይህ ነገር እንዳንመሳሰል አድርጎ አንድነታችንን ኣናግቷል;; አንድ እናት ልጆች ሆነን ሳለ ህጉ አመሳሶ ካመጣ ቅናት እና ተስፋ ማጣት ይከቡናል እነዚህ በሽታዎችም ለመፈራረስ ያቀብሉናል;;
     እንግዲህ አንድ ነን ስንል እነዚህ ከፍ ሲል ያዝ ለቀቅ እያረግን የተዎያየንባቸው 4ቱን ኢለመንቶች በእኩልነት ስንጋራ የምንፈጥረው የወል ስም ነው;; ይህ የወል ስማችን ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት ይባላል;;ይህ ስማችን የአንድነታችን አርማ የእኩልነታችን  ማህተም ነው;;ዜግነት የምንለውም ባለቤትነትን ሲያሳይ የነዚህ ጉልህ የኢትዮጵያ ስሪቶች ተጋሪ መሆናችንን የሚያረጋግጥ መብት ነው;;
ጎበዝ;;አሁን አሁን የሃገራችን ጉዳይ የሚያሳስበን ከነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች አንጻር ስናይ ነው;;ክፖለቲካዊ ጥያቄ የዘለለ ትልቅ ስጋት ገጥሟታል አገራችን;;የኢትዮጰያ አስተዳደር ጥያቄ አንባ ገነናዊ አስተዳደር የሚለው አገላለጽ አይመጥነውም ;; ከዚህ በላይ የሃገር ኢለመንቶችን ስራዪ ብሎ የሚያጠፋ መንግስት ለመሆኑ ምን ስም አለው?;;በአለማችን ታሪክ ብዙ ጨቋኝ ነገስታት እና ዲክተተርስ ተነስተዋል አሁንም አሉ;;ከሩቅ ጊዜ ታሪክ ስናይ ቻይናው የጥንት ንጉስ ብድግ ብሎ እጅግ ብዙ ሰው ያለቀበትን ግንብ አሰራ በወቅቱ ትርጉም የለሽ ቢሆንም አሁን ግን ከዚህ ግንብ ቻይናዊያን ከፍተኛ ገቢ ያገኙበታል;;ብዙ ቱሪስቶችም ለማየት ይጓጓሉ;;የግብጹ ንጉስ ደስ ሲለው ጊዜ   ሜቱን ለማርካት ያንን ጡብ አሰራ በዚያን ጊዜ ብዙ ሰው አለቀ ብዙ ሰው አካለ ስን ኩል ሆነ ብዙዎችም አነቡ ይሁን እና ዛሬ ልጆቻቸው ይህንን ጡብ ላማየት ከሚመጡ ቱሪስቶች የሚዝቁት ብር አያሌ ነው;;የኢትዮጵያን ያሁን ሁኔታእድገትአቅጣጫ ምን ይሏል? ቢያንስ ያሁኑ ትውልድ ተጎድቶ ለሚመጣው እየሰራን ነው እንዳይባል ዋና ዋና የሃገር ኢለመንቶችን ሲያናጋ ይታያል;;ቁዋሚ የሆነ ለትውልድ የሚያልፍ መሰረተ ልማትም አይታይም;;

 ምን እናድርግ ታዲያ? የተግባር ሰው ለመሆን
መንግስቱ ጠብ መንጃውን አቀባብሎ ወንድ የሆንክ ተጠጋኝ የሚል ይመስላል;; እሱ ባለብርት ሆኖ ሌላው ልምጭ ሳይዝ የጀግንነቱን የመጨረሻ ጫፍ እንደተቆጣጠረው ቆጥሮ ቁጭ ብሏል;;በነጻ ትግል ሜዳ ላይ ለውድድር ከቀረቡት ታጋዮች መካካል አንዱ ታጋይ ክላሽ ይዞ አንዱ ደሞ ባዶ እጁን ለትግል የቀረቡባት ምድር ትመስላለች ኢትዮጵያ;;እንዲህ አይነቱ የትግል በተፈጥሮ የማይገናኝ የፖለቲካ ትግል ስልት ልዩነት ሲታይ የሃገራችን ፖለቲካ የውጥረት ጥግ መምታቱን ያሳያል;;ውጥረት ደግሞ በተፈጥሮው አይቀጥልም;;ታዲያ  የሃላፊነት ስሜት እንዳለው ዜጋ ተደራጅተን ከምንታገለው ትግል ጎን ለጎን ምን እያደረግን እንቆይ ? እነዚህን የሃገር ዋልታና ማገሮች እንዴት እንጠብቅ ብልን መጠየቅ የፖለቲከኞች ጥያቄ አልሆነም;;ችግሩ የየ ፖለቲካ ጣጣ ቢሆን አብዛኞቻችን ችላ ባልን;; ግን አልሆነም እና የዜግነት የግለሰብ ንቅናቄ አስፈላጊ ሆኗል;እንግዲህ ከዚህ መንግስት ሴራ በላይ የሃገርችንን ኢለመንቶች  ስንጠብቅ መቆይት ውጥረቱ ሲበጠስ የዚህ መንግስት ተጽእኖ ኢንደሰንፍ ማድረግ ይቻላል;;በመሆኑም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የዜግነት ትግሉን የሚታገልበት አንዱ መንገድ እሴቶቻችንን በመጠበቅ እና የሃገራችንን ኢለመንቶች በመንከባከብ ነው;; የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆንም አልሆንም ትግሉ የሁላችን ነው;; በመሆኑም  በእለት ከእለት ህይወታችን የሚከተሉትን ለማድረግ እንትጋ;;

   1) ታሪካችንን በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ የመጠበቅ ባህል እናዳብር;;የታሪክ መጻህፍቶችን እናንብብ;;ለልጆቻችን ታሪካችንን እናስተምር;;ታሪካችን የሁላችን የኢትዮጵያዊያን መሆኑን በተለያየ አጋጣሚ ክምናገኛችው ኢትዮጵያውያን ዎገኖቻችን እንጫወት;; ጸሃፊዎች ታሪካችንን ይጻፉ ዘፋኞች ታሪኮቻችንን ይዝፈኑ ታሪክ ለሰሩ አባቶች ተገቢ ክብር መስጠት ታሪካችንን በቤታችን ግድግዳ መለጠፍ;;ሰአሊዎች ኢትዮጵያን የታሪክ አንድነት የሚያሳይ ስእል ይሳሉ;;
2)ማህበራዊ ካፒታላችንን መንከባከብ;;በገዢው መንግስት የዘር ፖለቲካ ሰለባ እንዳንሆን ራሳችንን መጠበቅ;;ማህበራዊ ድራችንን ወደ ሁሉም ኢትዮጵያ ልጆች ማድራት;; ኢትዮጵያን የተለያዩ አለባብስ አመጋጋብ ቋንቋ በመለማመድ እና በመቀባበል ትስስራችንን ፍቅራችንን መግለጽ እርስ በርስ መተማመን ማሳደግ ;;ይህ የግለሰብ አስተዋጽኦ ተደምሮ ሃግራዊ ይዘት እንደሚኖረው ራሳችንን ማሳመን;;የግል አስተዋጽዎአችንን አለመናቅ;;
3) የመሬት አንድነታችንን በተመለከተ ከአንዱ የሃገራችን ክፍል ወደሌላው ሄደን ስንኖር ውጪያዊነት እንዳይሰማን ራሳችንን መጠበቅ;;   ሁሉ የኢትዮጵያ ግዛት የኔ ነው የሚል የዜግነት መብታችንን መንከባከብ;;ለልጆቻችን ፍቅረ- መሬት እንዲያዳብሩ ማስተማር;;   ድንበራችን ሲነካ እውነተኛ የፖለቲካ ድርጂቶች የድረስ ጥሪ ሲያሰሙ አስተዋጾ ማድረግ;;
4)ፍትህን ለግላችን መለማመድ;;በተደጋጋሚ ከደረሰብን ጭቆና የተነሳ ሊከሰቱ የሚችሉ ባህርያት አንዳይታዩብን መጠንቀቅ;;
መተማመን ብዙ አለመጠራጠር ግን ጥበበኛ መሆን;; ውሽት ከማስመሰል መራቅ;; እነዚህ ሁሉ ጭቆና የሚያመጣችው በመሆናቸው ራሳችንን ስሜታችንን መፈተሽ;;በግል ህይወታችን በየማህበሮቻችን ፍትሃዊንትን ማሳደግ;;በተለይ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በየማህበሮቻቸው ነጻ ምርጫን ፍትህን መለማማድ;;
እንዲህ በግለሰብ ደረጃ ኢትዮጵያዊነትን ስንጠብቅ ቀጥሎ የሚመጣውን የሃገራችንን እድል አሳምረን እየሰራን ያለን ሃላፊነት የተሰማን ዜጎች እንሆናለን ማለት ነው;;ይህ በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው የኢትዮጵያን እሴቶች  የመጠበቅ ንቅናቄ ተደማምሮ ሃገራችንን በዚህ ማእብል መሃል እንደ መልህቅ ሆኖ ያቆማታል;;

                                           

                      geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...