Thursday, June 28, 2012

የነገይቱ ኢትዮጵያ ነገር

የኢትዮጵያን መጻኢ እድል በሚመለከት ለመናገር ሲነሱ የሚያስፈራ ነገር ኣለ። ይሄውም ስለ ነገ ለመናገር ተለዋዋጮቹን ብዙና ውስብስብ ኣድርገን ስለምናይ ኣንዳንዴም ጉዳዩን ያለ ቅጥ በማግዘፋችን  ኣንዳንዴም ትህትና የመሰለ ነገር ስለሚሰማን ይሆናል። ይህ ሁሉ ግን ተላላ የሚያደግ ይመስላል።

በዚህች ኣጭርዬ ጽሁፍ የኢትዮጵያን የነገ ህይወት ዛሬ እናያለን። የነገይቱን ኢትዮጵያን የምናይበት መነጽር ወሰብሰብ ያለ ጥናት ኣድርገን ሳይሆን ኣንድ የተፈጥሮ ህግ መስኮት ኣንገታችንን ብቅ ኣርገን ነው። ህግ በርግጥ ነገን ያሳየናል።  ህጉ በኢኮኖሚው፣በፖለቲካውና በማህበራዊ ኑሮ የኢትዮጵያን የነገ ይዘት ቁልጭ ኣርጎ ሳያዳላ ይነግረናል።

ኣነሳሳችን ኢትዮጵያ እንዳገር ወደፊት ምን ትመስላለች? የሚል ጠቅላላ ይዘት ያለው በመሆኑ የፖለቲካውን ቅኝት ዜማ ማየት ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ካቆሟት ዋና ዋና እግሮች (radicals) መካከል ኣንዱና ዋናው የመሃል እግር የፖለቲካ ውቅሩዋ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙህ ተፈጥሮ ያላቸው ሃገሮች የሃገር መቁዋጠሪያቸው ይሄው የፖለቲካ መዋቅራቸው ነው። በመሆኑም ከፍ ሲል ባነሳነው የተፈጥሮ ህግ መሰረት የኢትዮጵያን የነገ ህይወት ባጭሩ ለማየት ኣጠቃላይ የፖለቲካውን ጨዋታ መንፈስ ከህጉ ፊት ለማቅረብና ለማስተያየት እንነሳ።

ህጉ ምን ኣለ ምን ይላል?
ገበሬው የዘራውን ያጭዳል ይላል

መቼም ዛሬ በቆሎ የዘራ ገበሬ ነገ ጤፍ ኣጨዳ ኣይወጣም። ዛሬ ገብስ ያዘመረ ገበሬ የመኸር መሰብሰቢያው ጊዜ ሲመጣ ወይን እለቅማለሁ እያለ ኣያልምም፤ ኣያስብም። የተፈጥሮ ህጉ ኣለና የዘራውን ያችኑ ያጭዳል።  የምርቱ መጠን እንደ ግብዓቱ ይነስም ይብዛ የሚያጭደው ግን የዘራውን ነው።

የዚህን ህግ መነጽር ብድግ ኣርገን የኢትዮጵያችንን የነገ ህይዎት ስናይ ዘሩን በመጀመሪያ እናስባለን። ጉደኛው ህወሃት ስልጣን ከያዘ ወዲህ ሲያዘምር የነበረውና እያዘመረ ያለው ምንድነው፧ የፖለቲካ ቅኝቶቹ ድምጽ ምን ምን ይጫወታል ስንል መለያየት፣ ጥላቻ፣መከፋፈል፣ መራራነት፣ስግብግብነት፣ ጠባብነት ወዘት ናቸው። እንግዲህ ባነሳነው የማመሳከሪያ ህግ መሰረት የጀማመርነው ኣጨዳም ሆነ ወደ ፊት በሰፊው የምናጭደው በኣይነት ያንኑ የተዘራውን በመሆኑ በዚህ ህግ መሰረት ኢትዮጵያ ስትታይ ነገ ፈርሳለች።

ይሄ ህጉ የሚነግረን ደርቅ እውነት ነው። ህጉ ኣይፈራም ኣያዳላም።ግብዝነትም የለውም። በዚህ ህግ መሰረት ኢትዮጵያን ከነ ሙሉ ክብሩዋ ነገ ኣናያትም። እንክርዳዱ ዘር ኣድጎ ላጨዳ ሲደርስ በጠንካራው ክንዳችን ስንዴ ኣናደርገውም። ይህን ህግ የመቀልበስ መለኮታዊ ተፈጥሮም የለንም።

ምንድነው ታድያ ተስፋው፧
ይሄ ተገቢ ጥያቄ ነው። ኣንዳንድ መሬት ልግመኛ ነው። እምቢ ኣላበቅልም ይላል። በዚህ ጊዜ ዘሪው ይከስራል። ያ የመዝራትና የማጨድ ህግ ያልነው ለካ በዚህ በኩል ይሰበራል። ግሩም! እንዲህ ከሆነ ዘንዳ የፖለቲካው እርሻዎች እኛ ጭቁን ተራ ህዝቦች ነን። ፖለቲከኛው መከፋፈል ፣ ስግብግብነት፣ጥላቻ ፣ ጠባብነት ባንድም በሌላም መንገድ ሲዘራ እምቢኝ ይህን ኣላበቅልም ኣላሳድግም በማለት ያን ህግ ማቋረጥ ይቻላል ለካ። እንዴውም በተቃራኒው የኣንድነትን የመቻቻልን የፍቅርን ዘር በራሳችንና በቤተሰባችን እያዘመርን የነገይቱን ኢትዮጵያን ማትረፍ እንችላለን። ለ ወያኔ ፕሮፓጋንዳ በቃ እንቢኝ በማለትና ለተዘራው ዘር ምቹ ባለመሆን እንዴውም በተቃራኒው በማፍራት የነገይቱን ኢትዮጵያን በእግሯ ማቆም የቻለ ጀግና ትውልድ ተብለንም በታሪክ መዝገብ እንኖራለን። ተስፋው ይሄ ነው።
                       
                       
 እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ገለታው ዘለቀ
                       geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...