Friday, June 24, 2022

 

       ኢትዮጵያ በወሳኝ የሽግግርና የታሪክ መታጠፊያ ምእራፍ ላይ

                                                                                    

                                                        ገለታው ዘለቀ

 

                                መግቢያ

የዚህ ጽሁፍ አላማጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ስልጣን መልቀቅ አስፈላጊነት ላይ ብሎም የተውጣጣ የሽግግር መንግስት የመመስረት ሃሳብ ወቅታዊነት እና አስፈላጊነት ላይ በብርቱ መሞገት ነው። በመሆኑም በዚህ ትንታኔ ውስጥ የሽግግር መንግስት ጽንሰ ሃሳቦችን እንደ ዳራ ትንሽ ለመነሻ በማንሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ባስቸኳይ የሽግግር መንግስት የማቋቋም አስፈላጊነት ላይ በአምክህኖት እንሞግታለን። የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ዋና ዋና ተግባራት፣ እድሜው፣ ቅርጽና ይዘቱ፣  ሊገጥሙት የሚችሉትን ፈተናዎችና የጥንቃቄ ሃሳቦች እንሰነዝራለን። ይህንን ሃሳብ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራንና ህዝቡ ትኩረት ሰጥቶት የተሳካ የሽግግር መንግስት በመመስረት ሃገራችን መረጋጋት ውስጥ ገብታ ወደ ተሻለ ሰላምና ዴሞክራሲ እንድትራመድ ውይይት ያጭራል ብለን እናምናለን።

 

 

            የሽግግር መንግስት ምንነትና የኢትዮጵያ  ያልሰመሩ ሽግግሮች

የሽግግር መንግስት ታሪክ ከሰው ልጆች የመንግስት ምስረታ ታሪክ ቀጥሎ የኖረ ነው። ቅርጹ፣ ይዘቱ፣ ስያሜው ይለያይ እንጂ አላማው አንድን ሃገራዊ ህብረት ከኪሳራ ታድጎ የረጋ መንግስት መስርቶ ወደ ልማትና ሰላም ለማዘንበል ነው። የሽግግር መንግስትን አንዳንዶች የአደጋ ጊዜ መንግስት (emergency government) ይሉታል። እውነት ነው። ሃገር የህብረት መናጋት አደጋ ሲያጋጥማትና ሲያንዣብብባት የሚፈጠር መንግስት ሲሆን ሃገሮች ይህንን የአደጋ ጊዜ መንግስት በማቋቋም አንዳንዶች ይህንን የጽሞና ጊዜ ተጠቅመውበት የተሳካ ሽግግር ያደርጋሉ አንዳንድ ሃገራትም ደግሞ ሳይሳካላቸው እየቀረ ብዙ ጊዜ እየወደቁ የተነሱበት ሁኔታ አለ። በታሪካቸው ሶስት አራት ጊዜ የሽግግር መንግስት እየመሰረቱ ወድቀው እየተነሱ ሽግግራቸው የተሻለ ደረጃ የደረሰላቸው ሃገራትም አሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ 1960ዎቹ የነበረው የሽግግር ሃሳብ ሃገሪቱ ከዘውዳዊ አገዛዝ ወደ ሪፐብሊክ እንድትሻገር በተፈጠረ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያን ወቅት ቀስ እያለ ሳይታሰብ ቤተ መንግስት ገብቶ ንጉሱን ከስልጣን ያወረደው ደርግ ራሱን የሽግግር መንግስት ብሎ ሰይሞ ከአመታት በሁዋላ ደግሞ የሽግግር ጊዜው በተሳካ ሁኔታ እንዳበቃ ገለጸ። ይህ መንግስት ለንጉሱ መውረድ ምክንያት ናቸው የተባሉትን ችግሮች ሲደግም፣ እንዳንድ አዳዲስ ችግሮችን ጨምሮ ሃገር  ሲያምስ ቆየና ህወሃት ኢህዐዴግ 1983 አመተ ምህረት አዲስ አበባ ሲገባ ሌላ የሽግግር መንግስት መቋቋሙን ገለጸ። ልክ ደርግ ንጉሱን ጥሎ ራሱን የሽግግር መንግስት ብሎ አውጆ ሁዋላ የሽግግር ጊዜ አልቋል እንዳለው ህወሃት የመራው ኢህአዴግም እንደዚሁ ራሱን የሽግግር መንግስት ብሎ አመታት ቆየና አሁን የሽግግር ጊዜው አልቆ የረጋ ስርዐት መስርተን ወደ ፊት እየሄድን ነው አለ። ህወሃት ኢሃዴግ ደርግ ሲሰራው የነበረውን ግፍ በሙሉ ሰርቶ ተጨማሪ ግፎችን ሲያበዛ ህዝብ ምርር ብሎ ተቃወመ። በዚህ ጊዜ ራሱ ኢህዐዴግ ሁለት አማራጭ ቀረበለት አንደኛው አማራጭ መለወጥና ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ ለውጦችን አድርጎ ራስን ማትረፍና የለውጥ አካል መሆን፣ ሁለተኛው ምርጫ የህዝብ ተቃውሞን እያፈኑ ጊዜ መግፋት የሚሉ ናቸው። በዚህ መሃል አንደኛው አማራጭ የብዙ ኢሃዴጎችን ቀልብ ሳበ። ምንም እንኳን የህዝቡ የለውጥ ጥያቄ በሚገባ ባይገባቸውምና በህዝብ ጥያቄ ልክ ራሳቸውን ለለውጥ ባያዘጋጁም ነገር ግን ራስን ከመጥፋት ለማዳን ሲባል የፖለቲካ አክሮባቶችን በመስራት መቀጠልን የፓርቲው በአብዛኛው አባል የመረጠ ይመስላል።

 

የሚገርመው ነገር  ኢትዮጵያ ውስጥ በህወሃት ኢህዐዴግ ስርዐት ላይ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲነሳ ይህ የህዝብ ተቃውሞ በአለም ላይ ብዙም ያልታዩና ያልተለመዱ ክስተቶችን ሲያስተናግድ ነበር። በብዙ ሃገራት ታሪክ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ምርር ብሎ ሲነሳ ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አሽቀንጥሮ ይጥለዋል። ለምሳሌ ቱኒዚያን፣ ሱዳንን ማንሳት እንችላለን። ባለፉት ጊዚያት ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቡ ምርር ብሎ ከኢሃዴግ ጋር ሲታገል የህዝቡ ትግል ገዢውን ፓርቲ እጁን እየጠመዘዘ ለውጥ ለውጥ ቢያሰኘውም ተቃዋሚውን ግን ሲያሳድግ አለመታየቱ የኢትዮጵያን ህዝባዊ አመጽ ፍሬ ከብዙ ሃገራት ይለየዋል። ህዝቡ ምርር ብሎ በሚታገልበት ሰዐት ሰማያዊ ፓርቲ ፈረሰ፣ አንድነት ፈረሰ፣ መኢዐድ ብዙ ፈተና ውስጥ ገባ፣ ሌሎች ተቃዋሚዎች ፈረሱ። በህዝባዊ ተቃውሞ መሃል ተቃዋሚው እየፋፋ እየፋፋ ሄዶ ለሽግግር ጠንካራ ጎን ያለው ሃይል ሆኖ እንደመውጣት ተቃዋሚው መፍረሱ የሚያሳየው በትግላችን ጊዜ አንድ የፖለቲክ ሻጥር (conspiracy) መኖሩን ነበር።

ታዲያ ይህ ሻጥር  የኢትዮጵያ የለወጥ ሽግግር  በአንድ የኢሀአዴግ ክፋይ ላይ ብቻ እንጠለጠለ። ይህ ሂደት በቀጭን ገመድ ላይ የመሸጋገር ያህል የሽግግሩ እድልን በጣም ከባድ አደረገው።  ከኢሃዴግ የተገነጠለው የነዶክተር አብይ ቡድን ተቃዋሚውን ውስጥ ለውስጥ እያዳከመ መጥቶ በህዝብ ፊት በአንጻራዊነት ወፍራምና ለተፈላጊው ለውጥ ጫንቃና ትከሻው ያለው መስሎ ታየ።  በየመድረኩ እነ ዶክተር አብይ እመኑኝ አሻጋሪ ነን አሉ። ይህ የኢሃዴግ ክፋይ ራሴን እየለወጥኩ ነው እያለ የለውጥ ተስፋ ለህዝቡ መግብ ለነ ዶክተር አብይና ለነ አቶ ለማ መገርሳ መድረኮችን እያመቻቸ  በጎን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሙሉ እያዳከመ እየደቆሰ እንደመጣ ብዙዎች  አላሰተዋሉም ኢህአዴግ የገጠመውን ይህንን ከባድ ህዝባዊ አመጽ የሚወጣው በመጋፈጥ ሳይሆን በመገለባበጥ መሆኑን በአብዛኛው ስላመነበት በአንድ እጁ ተቃዋሚውን እያፈረሰ በሌላ በኩል እነ ዶክተር አብይንና ለማ መገርሳን የለውጥ ሰባኪዎች አድርጎ ለህዝብ ማሳየት ጀመረ።  ህዝቡም ለለውጥ በጣም መሳሳቱ የተነሳና በህወሃት ላይ ጥላቻ ስላደረበት እነ ዶክተር አብይ አንዲት ኢትዮጵያ ሲሉ ፈዝዞ ማዳመጥ ጀመረ። ተቃዋሚው ይበረታ ዘንድ ድጋፍ ከመስጠት ከኢሃዴግ መሃል መለወጥ ፈልገናል የሚለውን ሃይል አብዝቶ መደገፍ ጥበብ አድርጎ ብዙ ሰው አመነ። ሰሞኑን ስለ አንድነት ሲስብኩ የነበሩት አቶ ለማና ዶክተር አብይ ስልጣን ያዙ ሲባል ደግሞ ሁሉም  ጭብጨባውን አቅልጦ አንዲት የህገ መንግስት አንቀጽ መሻሻሉን ሳያረጋግጥ ድጋፉን ለኢሃዴግ ክፋይ ብቻ ሰጠና ወደየ ቤቱ ገባ። ይህ ወቅት የሽግግር መንግስት መስርቶ በረጋ ሁኔታ መሸጋገርን የሚጠይቅ የታሪክ መታጠፊያ ቢሆንም ራሱ የኢሃዴግ አካል የሆነው የነ ዶክተር አብይ ቡድን የሽግግር መንግስት መመስረት አያስፈልግም እኔ የምመራውን መንግስት እንደ ሽግግር መንግስት ቁጠሩት፣ የሽግግር መንግስት እንፍጠር ብንል የረባ ፓርቲ የለም በማለት ሲናገሩ ህዝቡም በአብዛኛው ማለት ይቻላል ተቃውሞ ሳያሰማ ቀረ። ተስማማ። ጥቂት ሰዎች የሽግግር መንግስት ይቋቋም ቢሉም ሃሳባቸው ተደማጭነት አጣ። እንዴውም ዱላ በዛባቸው። ታዲያ ይህ ወቅት ብዙዎች ግልብ ስሜትን ይዘው ተነስተው ሃገሪቱ ያለ ሽግግር መንግስት በነ ዶክተር አብይ ትሻገራለች እያሉ መስበካቸው የታሪካችን አንድ ትልቅ ጥፋት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን የሽግግር መንግስት ጥያቄ መዝለላችን  እንደ ሃገር በታሪካችን ውስጥ ተላላ ጊዜ ተብሎ ወደፊት በታሪክ መነሳቱ አይቀርም።

እንግዲህ ከፍ ሲል እንዳነሳነው ኢሃዴግ የህዝብን ተቃውሞ መቋቋም ሳይችል ሲቀር ራሴ ተገለባብጬም ቢሆን  ፍሴን አድኜ ይህቺን ሃገር መምራት አለብኝ ብሎ እንደተነሳ ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው አይነት ብዙዎች ረገብ ብለው ይህንን መንግስት ማየት ጀመሩ። ይህ አካል ግን  ሃገሪቱ እያማጠች ላለችው ስርዐታዊና መዋቅራዊ ለውጦች ምንም ሮድ ማፕ አልነበረውም። ቀደም ሲል ሲምልና ሲገዘትበት በነበረው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትምህርቱና በአዲሱ የህብረተሰብ ለውጥ ፍላጎት መካከል ያለው ቅራኔ ራሱን ይዞ ያንገጫግጨው ጀመር። ህዝብን ለማስደሰት በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ...... ከማለት ባሻገር በተለይ ሃገሪቱን ለሚያምሳት የብሄር ፖለቲካ ጉዳይ ግልጽ አቋም ሳይኖረው ቆየ። በአፍላው ከህዝብ ጋር ሊፈቱ የሚገባቸው መዋቅራዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ምንም ችግር ፈቺ  ሳይሆን ቀረ። ሃገሪቱ ባለችበት መዋቅራዊና ስርዐታዊ ሽብሮች (structural and systemic violence) ላይ ተጥዳ እንድትቆይ ሆነች ። የለውጥ ሃዋርያ ነኝ የሚለው የነዶክተር አብይ ቡድን መዋቅራዊ ለውጦችን ሳያመጣ ቀርቶ ውሎ ባደረ ቁጥር በህዝቡ ዘንድ ግርታን ጥርጣሬን አመጣ። ነገሮች እየገፉ ሲሄዱ፣ ህዝቡ በቃላት ተስፋ ብቻ ሲውል ሲያድር ጊዜ ማጉረምረም ተጀመረ። ትንሽ ቆይቶ ራሱ ኢሃዴግ ምንም ስርዐታዊ ለውጥ ሳያመጣ ራሱን ውሁድ ፓርቲ ነኝ ከዛሬ ጀምሮ ብልጽግና ተብያለሁ ብሎ ቁጭ አለ። በዚህ ውህደት ውስጥ ህወሃት ራሱን አግልሎ ከዋለ ካደረ በሁዋላ ነገሮች እየከፉ መጥተው በረጅም ጊዜ ታሪካችን የማናውቀውን ከፍተኛ ውጊያ በሰሜን በኩል እያካሄድን እንገኛለን። ይህ ውጊያ በሁሉም አቅጣጫ ደም እያፋሰሰ የሃገርን ሉዐላዊነት ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥዶ ይገኛል። እንግዲህ ብልጽግና የተዋሃድኩ ሃገራዊ ፓርቲ ነኝ የሚለው ውህደትን በማይፈቅድ ህገ መንግስትና የፖለቲካ ውህደትን በማያስተናግድ የፌደራል ስርዐት ላይ በመሆኑ ፓርቲው ውህደት አድርጊያለሁ ቢልም ወደ ተግባር ሲመጣ ግን ራሱን የጉራጌ ብልጽግና፣ የአማራ ብልጽግና የኦሮሞ ብልጽግና፣  ወዘተ በማለት መተዳደር ጀመረ። አንድ የጋራ የዳቦ ስም ከማውጣት ባሻገር ይህ ፓርቲ የፖለቲካ ውህደት ማድረግ አልቻለም። እንዴውም ውሁድ የፖለቲካ ስብእና በማያስተንግድ ህገ መንግስትና የፌደራል ስርዐት ላይ ይህ የብልጽግና ውህደት ከባድ የስርዐትና የመዋቅር ግጭት ፈጥሮ ችግሮችን አባብሶ ቁጭ አለ። ፓርቲው የተዋሃድኩ ነኝ ቢልም በኢሃዴግ ጊዜ ከነበረው ልዩነት በበለጠ በውስጡ ልዩነቶችን አስፍቶ የሚኖር ፓርቲ ሆኖ ወጣ። ከፍ ሲል እንዳልኩት ይህ ፓርቲ ከመዋሃዱ በፊት የፌደራል ስርዐቱና ህገ መንግስቱ መሻሻል ነበረበት ነገር ግን  ብልጽግና ስርዐታዊ ለውጥ ሳያመጣ በመዋሃዱ ከፍተኛ ስርዐታዊና መዋቅራዊ ግጭት ውስጥ ገብቶ ቁጭ አለ።

 በሃገርችን ውስጥ የተፈለገው ለውጥ በጣም ወፍራም ሆኖ ሳለ ነገር ግን  በአንድ እንዲህ ባለ ቀጭንና ጠንካራ ባልሆነ ፓርቲ አመራር ላይ ወደቀ።  ይህ ፓርቲ ከሃገር ህልውና በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ ከብዙ ህዝባዊ ማእበል ውስጥ አክሮባቶችን ሰርቶ ራሱን ማትረፍ ነው።  

 ከመነሻ እንዳልኩት ፓርቲው ያለ ምንም ስርዐታዊ ለውጥ ውህደት መፈጸሙ አንዱ የመንገጫገጩ መነሻ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ይህ ፓርቲ ስልጣን ላይ እያለ ከአንድ ፓርቲ ፈርሶ በሌላ ፓርቲ መልክ ራሱን መግለጡ ደግሞ በጣም አሳዛኝ ነገር ነበር። ይህቺ ሃገር የማይሆንባት ነገር የለምና ችላው ትኖራለች እንጂ አንድ ፓርቲ የመንግስትን ስልጣን ከያዘ በሁዋላ መቅለጥ፣ አዲስ ፓርቲ መመስረት አይችልም። እውነት ነው ፓርቲዎች የመንግስት ስልጣን ሳይዙ ራሳቸውን ማቅለጥ፣ ማዋሃድ፣ የርዕዮትና የስያሜ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን  ስልጣን የያዘ አንድ ፓርቲ እንዲህ አድርጎ ህዝብ ጫንቃ ላይ እያለ ፈርሶ መደራጀትን ሊያስብ አይችልም ነበር። እውነተኛ ምርጫ ቦርድ ቢኖረን ኖሮ ይህንን ተግባር አይቀበልም ነበር። የሆነ ሆኖ ፓርቲው ብዙ ግጭቶችን ይዞ የተንሳ ስለነበረ የሃገሪቱን ለውጥ ለመምራት ብርክ ያዘው። ከህወሃት ጋር የተፈጠረው ጦርነት በአንድ በኩል፣ የተፈጠረው ስርዐታዊ ሽብር በሌላ በኩል ወጠሩት፣ የህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችና የሃገሪቱ ከባባድ ለውጦች በየቀኑ ይህንን ፓርቲ በዝረራ ይጥሉት ጀመር። ሰላም ማስከበር ተሳነው፣ በክልሎች መካከል ጥርጣሬ በዝቶ ወታደር አሰልጥነው ለእርስ በርስ እልቂት የተፋጠጡ መሰሉ። ማእከላዊ መንግስት አቅሙ ደክሞ የክልሎች ጉልበት አየለ። የጋራው ቤታችን ፈራ።  የኑሮ ውድነት፣ የስርዐት መነቃነቅ፣ መፈናቀል፣ ረሃብ፣ ሙስና፣ የብሄር ጥላቻ እያደጉ መጥተው ዛሬ በዚህ ሁኔታ ልንቀጥል የማንችልበት ሌላ የታሪክ መታጠፊያ ምእራፍ ላይ አንሳፎ አምጥቶ አስቀምጦናል።

ተመልከቱ፣  በ2013 ዓመተ ምህረት ብቻ በውስጥ መፈናቀል ኢትዮጵያ የአለምን ሪኮርድ ሰብራለች ። በዚህ አመት 5.1 ሚሊዮን ህዝብ በገዛ ሃገሩ ተፈናቅሎ መግቢያ አጣ። ይህ ህዝብ የጂቡቲን፣የኢስዋቲኒን፣የሞሪሽየስን ፣የኢኳቶሪያል ጊኒንና የኮሞሮስ ሃገራት ህዝቦችን በሙሉ ተደምሮ ያክላል። የአምስት አፍሪካ ሃገራትን ቁጥር የሚያክል ህዝብ በምድረ ኢትዮጵያ ተፈናቅሏል።  ይህ ቁጥር ከፍ ሲል እንዳልኩት የአለምን የውስጥ መፈናቀል ሪኮርድ ታሪክ የሰበረ ነበር። ከቶ ከዚህ የከፋ ነገር ምን አለ? ትናንት በወለጋ አማሮች ላይ የታየውን ዘር ተኮር ግድያን ጨምሮ በየወሩ አንዳንዴ በየሳምንቱ የዘር ማጥፋት ዜና መስማት የተለመደ ሆኗል። በቅርቡ በሶያማ ከተማ ብዙ ጉጂዎች በማንነታቸው ተገድለዋል፣ ቀደም ሲል ቡርጂዎች በማንነታቸው በተደጋጋሚ ተገድለዋል፣ ኩሱሜዎች በማንነታቸው ተገድለዋል፣ እንዴውም አንድ የኩስሜ ቀበሌ ህዝብ እንዳለቀ መረጃዎች ያሳያሉ። ሰገን ህዝቦች በማያባራ እልቂት ላይ ናቸው። ጉማይዴ ሰላም ከራቀው ቆየ።  ቤንሻንጉል ጉሙዝ ወቅት እየጠበቀ በሚነሳ እልቂት ሺሆች አልቀዋል። ጋምቤላ ውስጥ እያሰለሰ በሚደረግ ጦርነት ሺሆች አልቀዋል። ኢትዮጵያዊያን ሶማሌዎች፣ አፋሮች፣ ኦሮሞዎች በዙር እያለቁ ነው። የትግራይ ህዝብ በጦርነት፣ በረሃብ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው የምድር ላይ ሲዖል ኑሮን ይኖራል። አማሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰላም አጥተዋል። በደራ የሚኖሩ አማሮች ሰላም አጥተው ተፈናቅለዋል። ብዙዎች ተሰደው እነዚያ ኩሩ ገበሬዎች ዛሬ አዲስ አበባ አካባቢ የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል። የአዲስ አበባ ህዝብ በኑሮ ውድነትና በስራ ማጣት እየተገረፈ ነው። ማክሮ ኢኮኖሚያችን በመዋቅራዊ ችግሮች ተተብትቦ ተይዟል። ኑሮ እያደር ቁልቁል ከሆነ ውሎ አድሯል። ብዙ ድሃ ህዝብ ሜዳ ላይ ጥለን ከባባድ ድሽቃዎችን በውድ ዋጋ እየገዛን እርስ በርስ እንጫረሳለን። በየቀኑ ለጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያወጣን ሚሊዩን ህዝብ ዳቦ አጥቶ የሚያድርባት ሃገር ሆናለች ኢትዮጵያ። ይህቺ ሃገር ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክማ የያዝነውን ለውጥ እንቀጥላለን የሚል መፈክር የሚሰማባት ሃገር ሞሆኗ ደግሞ ገራሚ ነው። ይህ ሁኔታ በዚህ ሊቀጥል አይችልም። አንድ ሃገር በእንደዚህ አይነት ከባድ ችግሮች ውስጥ ሲገባ በፍጥነት የፖለቲካ ለውጥ በማምጣት የሽግግር ጊዜን ማሰብ አለበት ።

ለዚህ ነው ዛሬ ከመቼም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚያስፈልግበት ወሳኝ ሰዐት ላይ ነን የሚያሰኘን።  ከላይ በለሆሳስ ያነሳነው መነሻ እንዳለ ሆኖ የሚከተሉት መሰረታዊ ምክንያቶች ሃገራችን ኢትዮጵያ ባስቸኳይ ወደ ሽግግር መንግስት ምስረታ እንድታመራ ያስገድዳሉ። እነዚህን ምክንያቶች ዝቅ ሲል እንወያይባቸው። ለምን የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል እንላለን? ፦

   

1.   የኢትዮጵያ ሽግግር ክብደትና ግዝፈት

 

የኢትዮጵያ የሽግግርና የታሪክ መታጠፊያ ጥያቄ እንደ ሌሎች ሃገራት ቀላል አይደለም። ስለ ኢትዮጵያ ሽግግር ስናስብ ይህንን ክብደት መመዘንና መረዳት ግድ ይለናል።  የብዙ ሃገራት የሽግግር መንግስት ጥያቄ የሚነሳው መሪዎች በሙስና ሲዘፈቁ፣ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት ሲሳናቸው፣ የዳቦ ዋጋ ሲጨምርና የኑሮ ውድነት ጥያቄ ሲመጣ፣ መሰረታዊ የዴሞክራሲና ሰባዊ መብቶች ጥሰት ሲያይል የሚፈጠር ጥያቄ ነው። ህዝቦች እነዚህ ችግሮች መከራ ሲያሳዩዋቸው መንግስትን በምርጫ ሳይሆን ባስቸኳይ መቀየር ይሻሉ። ምርጫ በዚህ መንግስት ዘንድ እውን እንደማይሆን ስለሚያምኑ ባስቸኳይ ይህንን መንግስት ከጫንቃቸው ላይ ማንሳት ይሻሉ።  በዚህ ጊዜ የሽግግር መንግስት ጥያቄ ይመጣል። ለምሳሌ ቱኒዚያን ብናይ ስራ አጥነት እየበዛ መልካም አስተዳደር እየተበላሸ ስለመጣ ህዝብ ተቆጥቶ ነበር። ኋላ ላይ አንድ ዩኒቨርሲቲ ጨርሶ ስራ ያጣ ወጣት ሱቅ በደረቴ ስራ እየሰራ ሳለ ኑሮው አልቃና ሲለው ጊዜ  ራሱን በእሳት አቃጥሎ ገደለ። በዚህ ጊዜ ቱኒዚያ ውስጥ አገሩ በሙሉ አበደ። ህዝቡ መሬት አንቀጥቅጥ አመጽ አነሳና የመንግስት ለውጥ አስከተለ። ሱዳን ውስጥ የዳቦ ዋጋ መጨመር ያስከተለው አመጽ አልበሽርን አውርዶ ሃገሪቱ ስለሽግግር እንድታስብ አድርጓል። ሽግግሩ እንከን ቢበዛበትም የህዝቡ ጥያቄ አልበሽርን አውርዶ  ለሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ እድል ፈጥሯል። ብዙ ሃገራት ጥያቄያቸው እንደነዚህ አይነት ሲሆን የኢትዮጵያ የለውጥ ጥያቄዎች ግን ከዚህ በጣም በጣም የከበዱ ጥያቄዎች አሉበት።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ከባድ ነው የሚያሰኘን ጥያቄው በአንድ በኩል የመልካም አስተዳደርና የኑሮ ውድነት ጥያቄ ሲሆን ሌላውና ዋናው ጥያቄ ደግሞ የመተሳሰሪያ መርሆዎች ክለሳ (revision of the main organizing principles ) ጥያቄዎች ይዟል። እጅግ መሰረታዊ በሆኑ የሃገር ምሰሶዎች ላይ የሃሳብ መሻሻልና ክለሳ የሚያስፈልጋት ሃገር ናት ሃገራችን። እንዲህ አይነት ለውጥ ደግሞ ከህገ መንግስቱ በላይ መተሳሰሪያ መርሆዎችን መርምሮና የተሻሉ መርሆዎችን አፍልቆ መግባባት ባሳዩ ሃሳቦች ዙሪያ መተሳሰሪያ መርሆዎችን መቅረጽና የህገ መንግስት ድንጋጌዎችን ማድረግን ይጠይቃል። ይህ ለውጥ በብዙ ሃገራት አይታይም። የብዙ ሃገራት ለውጥ ከዚህ በጣም ይቀጥናል። ከፍ ሲል እንዳልኩት የብዙ ሃገራት ጥያቄ ከሙስና ጋር ከመልካም አስተዳደር ጋር ብቻ የተያያዙ ናቸውና። የእኛ ሃገር የሃሳብ ክለሳ የሚደረግባቸው ጉዳዮች ቢያንስ  በጥናት የታዩ ሰባት ጉዳዮች አሉ። እነዚህ የሃሳብ ክለሳ የሚሹና ሽግግር የሚሹ  አጀንዳዎች፦

 

1.1.    የኢትዮጵያን ሃገራዊ ህብረት ፍጹምነት በሚመለከት።

 

አንዱ ዋና አጀንዳ የኢትዮጵያ ዘላለማዊነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት ጥያቄ ውስጥ ነው። የህብረታችን ልክ በመገንጠል የተወሰነ እንደሆነ ህገ መንግስቱ የሚደነግግ ስለሆነ ሃገሪቱ አሁን ባላት መተሳሰሪያ መርሆ መሰረት ህብረታችን ፍጹምነት የለውም። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ሁለት አይነት ሃሳቦች በገበያ ላይ አሉ። አንዱ ሃይል በኢትዮጵያ ፍጹነት ላይ ቀድሞውንም ድርድር አያስፈልግም ይላል። ሌላው ደግሞ የብሄሮች መብት ጥግ ነው አይነካም ይላል። በርግጥ ሃገራዊ ህብረቷን ፈራሽ አድርጋ የመሰረተች ሃገር በአለም ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ናት

ስለዚህ ህገ መንግስት ይሻሻልና ይህ መተሳሰሪያ መርሆ ተለውጦ ኢትዮጵያ ህብረቷን ወደ ፍጹም ህብረት እንድታሳድግ መነጋገርና ይህንን መተሳሰሪያ መርሆ ማስተካከል ይጠይቃል። በመሆኑም ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫየን አለች እንደሚባለው መጀመሪያ የኢትዮጵያን ዘላለማዊነት በሚመለከት ሽግግር ያስፈልጋል። አንዱ ትልቅ ሽግግር የሚባለው ይሄ ነው። ኢትዮጵያ የማትፈርስ ዘላለማዊ ሃገር መሆኗን በህገ መንግስቷ ለመጻፍ መነጋገር ያስፈልጋል። አንዱ ሽግግር ኢትዮጵያ ፈራሽ ናት ከሚል መተሳሰሪያ መርሆ፣ ኢትዮጵያ ከእግዚአብሄር በታች የማትከፋፈል አንድ ሉዓላዊት ሃገር ናት ወደሚል መተሳሰሪያ መርሆ የሚደረግ ሽግግር ነው። በዚህ መተሳሰሪያ መርሆ ላይ ከተስማማን በሁዋላ ይህንን ጉዳይ በህገ መንግስት ስንተክለው መዋቅራዊና ስርዐታዊ ለውጥ አደረግን፣ የመርህ ሽግግር አደረግን እንላለን። አንዱ ትልቁ የሚጠበቀው መዋቅራዊ ለውጥ ይሄ ነው።

 

1.2.    የቅርጸ መንግስትና የፌደራል ስርዐት ክለሳ

 

                ሁለተኛው ከባድና መሰረታዊ ለውጥ ደግሞ የቅርጸ መንግስትና    

የፌደራል ስርዐት ለውጦችን ይይዛል። ኢትዮጵያ ስትከተለው የቆየችው የፌደራል ስርዐት ከፍተኛ መንገጫገጭ ከመፍጠሩም በላይ ክልሎች ማንነቶችን ሳቢ ሆነው ስለተተከሉ ልዩነትን መሸከም አልቻሉም። እንዴውም ልዩነትን የሚገፉ ሆነው ተገኝተዋል። ይህንን በማየት ብዙዎች አምርረው ይህ የፌደራል ስርዐት መቀየር አለበት ክልሎች ተመሳሳይነትን የሚስቡ ሆነው መተከል የለባቸውም፣ የሚል ክርክር ያቀርባሉ። አንዳንዶች ይህንን ክርክር ይቃወማሉ። ስርዐቱ ላይ ዴሞክራሲ ማፍሰስ ነው የቀረን እንጂ የብሄር ፌደራል ስርዐቱ በራሱ ችግር የለውም ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ስርዐት ከዴሞክራሲ መርሆዎች አንጻር አይቶ ከብሄር ፌደራል ስርዐት ሃገሪቱ ካልተሻገረች ስርዐታዊ ግጭቱ ስለሚቀጥል የግድ ብሄራዊ መግባባት በዚህ ላይ መምጣት አለበት። የፖለቲካ ዩኒቶች ማንነትን የሚስቡ ሆነው የተዋቀሩበት ገመድ ተቆርጦ ዜጎችን ሁሉ ሳቢ ሆነው መተከል አለባቸው።  ርግጥ ነው ሃገሪቱ የብሄር ፖለቲካን ስትሻገር የማንነትን ጥያቄ የሚመልስ ቅርጸ መንግስት መፍጠር ግዴታዋ ይሆናል። ይህንን የሚያቻችል ኢትዮጵያን የመሰለ የፌደራል ስርዐት ለመቅረጽ መመካከር ያስፈልጋል። አንዱ ሽግግር ይሄ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ቅርጸ መንግስት ብሄራዊ መግባባትን ይሻል። የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀርን በሚመለከት፣ የህገ ትርጉም ስራ ጉዳይን በሚመለከት፣ ሃገሪቱ የምትከተለው የመንግስት ስርዐት ማለትም ፓርላመንታሪ ሆኖ ይቀጥል ወይስ ፕረዚደንሺያል የሚለው ጉዳይ ስምምነትና ሽግግር  ያስፈልጋቸዋል።

 

1.3.    የብሄር ማንነትና የብሄራዊ ማንነት መስመሮችን በሚመለከት

 

የሃገራችን ዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎች በአብዛኛው ግልጽነት ይጎድላቸዋል። ብሄር ከብሄር፣ ብሄራዊ ማንነት ከብሄር ማንነት ጋር የተሳሰሩበት መንገድ ብዙ ክለሳ ይጠይቃል። እነዚህ ጉዳዮች የጠሩ ብያኔዎችና የጠሩ የመሮጫ መሞች ሊበጁላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረግና የተሻለ መርሆ ቀርጾ ወደ ህገ መንግስት መቀየር ዋና የሽግግር ስራ ነው። ይህ ክለሳ ከባድ ለውጥ ነው።

 

1.4.    የቋንቋ አያያዝ በሚመለከት

 

በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ብዙ ቋንቋዎች አሉ። እነዚህን ቋንቋዎች እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? የሚለው ሃሳብ ትልቅ ጉዳይ ነው። ብሄራዊ መግባባትን ይጠይቃል። በቀላሉ በአንድ ፓርቲ ፖሊሲ የሚሰራ መሆን የለበትም። በጥናት ላይ የተመሰረተ ውይይት አድርጎ የቋንቋ አያያዛችን አንድ መስመር መያዝ ያስፈልገዋል። ይህም አንድ ትልቅ ሽግግር ነው።

 

 

 

 

1.5.    የብሄራዊ ምልክት ጉዳይ

 

ኢትዮጵያ መስማማት ካልቻለችባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ መፍታት አንድ ትልቅ ሽግግር ነው። ብሄራዊ ምልክት አንድ ፓርቲ ስልጣን በያዘ ቁጥር የሚቀይረው ጉዳይ ሳይሆን ቋሚነትን ይጠይቃል። ስለዚህ የጋራ መግባባትን ይጠይቃል። በሌላ በኩል የብሄራዊ እንስሳ ምልክታችን ላይ አዳዲስ አለመግባባቶች መጥተዋል። ዶክተር አብይ ወደ ቤተ መንግስት ሲገቡ ፒኮክ ይዘው መግባታቸውን ተከትሎ የብሄራዊ እንሰሳ ምልክታችን የአንበሳው ነገር  ብዙዎቻችንን አሳዝኗል።  ይህም ፈር መያዝ ስላለበት በውይይት የሚፈታ አንድ ሽግግር ነው። ብሄራዊ መዝሙራችን አንድ ወሳኝ ጉዳይ ነው። እንደ አንድ የሃገር ልጅ አንድ የጋራ ዝማሬ ያስፈልገናል። በዚህ ላይ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

 

1.6.    ያለፈ መጥፎ ትውስታን (past bad memories) ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መሰናክል እንዳይሆን ይህንን ምእራፍ በሆነ መንገድ መዝጋት አለብን። ያለፈውን እያነሳን ስናላዝን የምንኖር ሰዎች መሆን የለብንም። ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በተለያየ የካሳ ዘዴዎች ተጠቅመን መፍታትና መሻገር አለብን።

 

1.7.    የመሬት ላራሹ ጥያቄ

                     ይህ ከባድ ጥያቄ ብሄራዊ ምክክር ተደርጎበት አንዱ ሽግግር ይሄ

                     ጉዳይ ነው። የመሬት ፖሊሲ ፓርቲዎች በምርጫ በመጡ ቁጥር    

                     የሚቀይሩት ሳይሆን መሬት በግል ይያዝ ዘንድ ከፍተኛ መግባባት

                     ይጠይቃል። በአለም ላይ መሬት በመንግስት የተያዘባት ሃገር           

                   ኢትዮጵያ ብቻ ናት ። መሬት ከገበያ ስርዐት መውጣቱ በማክሮ      

                    ኢኮኖሚያችን ላይ ያለውን ኪሳራ ማየት፣ ከሁሉ በላይ ገበሬው

                    ይዞታ ማስፋት ስለማይችል ኑሮው ሁሉ ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ

                    እንዲኖር አድርጎታል። እርሻችን ሁለ-ገብ በመሆኑ ስፔሻላይዜሽን

                    እንዳያድግ አድርጓል። የመሬት ፖሊሲው ድህነትን አምጥቷልና

                    ተወያይተን በዚህ ላይ ሽግግር ያስፈልጋል።

                                                                                                       

እነዚህ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያን ሽግግር ጥያቄ ምን ያህል ከባድ እንደሆነና በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊመሩ እንደማይችሉ ያሳያሉ። ከዚህ በተጨመሪ የሚከተሉት ጉዳዮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንድንመሰርት የሚያስገድዱ ተጨማሪ ጉዳዮች ናቸውና ከዚሁ ቀጥለን እንመልከት።  

 

2.   የዶክተር አብይ መንግስት ቅቡልነት መውደቅና መክሸፍ

 

ሁለተኛው የሽግግር ሃሳብን እንድናነሳ የሚያደርገን አሳማኝ ነገር የዶክተር አብይ አመራር መክሸፍ ነው። ከፍ ሲል እንዳነሳነው ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ህዝብ ለለውጥ በጣም ጓጉቶ ነበር። እኒህ ሰው ህዝቡ ይፈልጋቸው የነበሩ የሽግግር ሃሳቦችን በተለያዩ ጊዚያት እያነሱ ተስፋ ስለሚሰጡ ለተወሰኑ ጊዚያት የብዙዎችን አመኔታ አግኝተው ነበር። ነገር ግን አንዳንድ በጣም አጥብቀው የሚመለከቱ ዜጎች ኢሃዴግ እለወጣለሁ ማለቱ እሰየው ነው ነገር ግን  በምንም አይነት መልኩ ብቻውን የሽግግር መንግስቱን ይምራ ብለን መፍቀድ የለብንም ብለው ነበር። ጨክነን የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ይኑረን የሚል ሃሳብ ያነሱ ነበሩ። ይሁን እንጂ በወቅቱ ይህ አሳብ ሰሚ አልነበረውም። ዶክተር አብይ ራሳቸው የሽግግሩን ስራ የሚሰሩ አሻጋሪ መንግስት ነኝ እያሉ ሲሰብኩ ነበር።

ባለሙያዎች የሽግግር መንግስት አይነቶችን በአምስት ይከፍሏቸዋል። እነሱም

1      አብዮታዊ የሽግግር መንግስት (ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በአመጽ ጥሎ የሚመሰረት የሽግግር መንግስት )

2      ስልጣን በመካፈል የሚመሰረት ሽግግር መንግስት (power sharing transitional government) ይህ አይነት የሽግግር መንግስት ስልጣን ላይ ያለው መንግስትና ተቃዋሚው ስልጣን ተጋርተው የሚመሰርቱት የሽግግር መንግስት ነው

 

3      ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ራሱ የሽግግር መንግስት ስራን ሲወስድ Incumbent provisional government ይባላል።

 

4      የባለሙያዎች ባለ አደራ መንግስት ( ይህ መንግስት የሽግግር መንግስትን ቦታ ይዞ በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ስልጣን አስረክቦ ይከስማል)

 

5      የባለ አደራ መንግስት(caretaker government) ይባላሉ

 

እንግዲህ ከፍ ሲል ከዘረዘርናቸው የሽግግር መንግስት አይነቶች የዶክተር አብይ መንግስት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ራሱን የሽግግር መንግስት ባለስልጣን አድርጎ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን የሽግግር መንግስት የሚመስል መንግስት ነበር የዶክተር አብይ መንግስት ማለት ነው።  ይሁን እንጂ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት የሽግግር መንግስት አይነቶች የተሻለው አማራጭ በፍጹም አልነበረም። ከፍ ሲል እንዳልነው ተፈላጊው ለውጥ የህገ መንግስት ማሻሻያ የሚጠይቅ ከባድ ለውጥ ስለነበረ አንድ ፓርቲ ያውም ከገዢው ፓርቲ የተፈረከሰ አካል ይህንን ግዙፍ ለውጥ ሊመራው እንደማይችል ግልጽ ነበር። ይሁን እንጂ ዶክተር አብይ የሽግግር መንግስትን ሃሳብ ሲበዛ ይጠላሉና እምቢኝ ብለው ሲቀጥሉ እነሆ ቃላት በተግባር የሚፈተኑባቸው ወራት መጡ። ይህ እሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ገና ሮድ ማፕ የሌለው በዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎች ላይ የጋራ አቋም የሌለው፣ የአማራ ብልጽግና ከኦሮሞ ብልጽግና በህገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር የሚለያዩ ሆነው፣ የኦሮሞ ብልጽግና ከትግራይ ብልጽግና የሚለይ ሆነው ሳለ ዶክተር አብይ አሁንም አሻጋሪ ነኝ እያሉ ህዝብን ለማደንዘዝ ይሞክራሉ። እያደር ህዝብ ሲታዘባቸው በየመድረኩ የሚናገሩት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የሚጋጭ ሆነ። ከፍ ሲል ባነሳናቸው ብሄራዊ አጀንዳዎች ላይ አቋማቸው አልታወቅ አለ። ስልጣን ላይ ለመቆየት ብቻ ህዝቡን የተወሰነ ጊዜ ደለሉ። አንድ ሃገር የተሻለ ሽግግር ለማየት አንድ አመት ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት የሚበቃ ሲሆን የኒህ ሰው አራት አመታት አመራር በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በሰኪዩሪቲው፣ በሁሉም መለኪያዎች ጉዟቸው ሁሉ ቁልቁል ሆነ። በአሁኑ ሰዐት እጅግ ብዙ ሰው ንግግራቸውን ማዳመጥ ከማይፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።  

አንዳንዶቻችን ገና እኒህ ሰው ወደ ስልጣን ሲመጡ ሽግግሩን በራሳቸው ይመሩታል ብለን አላመንም ነበር። ስለዚህ ባስቸኳይ ለሽግግር የሚረዱ ተቋማት እንዲመሰረቱ ጮኸናል። በዚሁ መሰረት የማንነት፣ አስተዳደርስና ወስን ጉዳዮች ኮሚሽን፣ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን እንዲቋቋሙ ተወሰነ። ይሁን እንጂ ገና እነዚህ ኮሚሽኖች ሲቋቋሙ ጀምሮ እንከን በእንከን ሆነው ተመሰረቱ። ይህ አልበቃ ብሎ አንድም ስራ ሳያስመዘግቡ ሁለቱም ኮሚሽኖች ፈረሱ። ይህ ችግር ለሽግግሩ ክሽፈት አንድ ማሳያ ነው። የዶክተር አብይ መሰረታዊ ችግር የተቋም ግንባታና ክትትል እንደሆነ በሚገባ አሳይተዋል። እኒህ ሰው በአብዛኛው የላንቲካ ስራዎች የሚማርኳቸው ሲሆኑ በሃገሪቱ ወሳኝ የመግባቢያ ጉዳዮች ላይ ጊዜያቸውን አያጠፉም። ውለው ሲያድሩ ነገራቸው ሁሉ እየቸከ እያቸከ መጣ። በለውጥ ፍላጎትና በስርዐቱ መካከል ያለው ግጭት ስርዐታዊ ሽብሩን እያፋፋመው ሄደና በታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ መፈናቀል፣ ጦርነት፣ ወሮበላነት፣ ዘረፋ፣ ስርዐት አልበኝነት ያለ መጥን አደገ። እኒህ ሰው በየቀኑ ቅቡልነታቸው እያዘመመ ሲሄድ ዘጭ ብሎ እስኪወድቅ ድረስ ዝም አሉ። እርቅና መግባባትን ማምጣት አልቻሉም። ነገሮች እየከረሩ መጥተው ዛሬ ዘር ተኮር ፍጅት የየሳምንቱና የየወሩ ዜና ሆኗል።

ዶክተር አብይ ስልጣን ሲይዙ የሽግግር አካል የሆነውን ብሄራዊ ምርጫን ለማድረግ ጠንክረው ይሰራሉ ብለው የታመኑባቸውን ሰዎች አሳፈሩ። በምርጫ ታሪካችን ውስጥ አሳፋሪ ነገሮች ሁሉ የታዩበት ቅድመ ምርጫ ጀመሮ ማጭበርበር የበዛበት ምርጫ አድርገው እንደተለመደው ወደ መቶ ፐርሰንት የተጠጋውን ወንበር ይዘው ምርጫ አደረኩ ተሻገርን ብለው አላገጡ። የተሻለ ፓርላማ ሳይመሰረት ቀረ። የኑሮ ውድነት ህዝቡን እየቀጣው ባለበት በዚህ ወቅት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። ምግብ ነክ በሆኑ ሸቀጦች ላይ እስከ 40 በመቶ ግሽበት ሃገሪቱን መታት ድሃው ኑሮውን ማሸነፍ ተስኖት መራራ ህይወት ይኖራል። ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋል እየተባሉ ቢጮህም ዶክተር አብይ ችላ ብለው አራት አመት ከቆዩ በሁዋላ አሁን የምክክር ኮሚሽን አቋቁመናል ብለዋል። ይህ ኮሚሽን ከአመሰራረቱ ጥያቄ ስላስነሳ ፓርቲዎች ቀጥታ ተሳታፊ ስላልነበሩ ከመነሻው በዛ ያሉ ፓርቲዎች በዚህ ኮሚሽን ላይ አመኔታ የለንም አሉ። ከሁሉም በላይ ሃገሪቱ ጦርነት ውስጥ ስለሆነች እርቅና ሰላም መጀመሪያ ይምጣና ወደ ምክክር እንሂድ የሚል ጥያቄ ተነሳ። ይህ ኮሚሽን በስሪቱ መንግስታዊ በመሆኑ የገለልተኝነት ጥያቄው በራሱ ብዙ አያራምደውም።

 

ከሁሉም በላይ ዶክተር አብይ የህዝቡን ሰላም ማስጠበቅ ባለመቻላቸው በየክልሉ ዘር ተኮት ፍጅት ስለበዛ እኚህ ሰው በፍጥነት ዘወር ብለው የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የብዙ ሰው ጸሎት ሆኖ እያየን ነው። በአጠቃላይ የዶክተር አብይ ቅቡልነት እጅጉን የወረደ ስለሆነ ከዚህ በሁዋላ ምን ይመጣ ይሆን እያሉ አፍጦ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ሃገር እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ፈጥኖ ስለሽግግር ማሰብ ያስፈልጋል። የዶክተር አብይ የለውጥ ጉዞ እንደ ከሸፈ ከሚያሳዩን ጉዳዮች መካከል አንዱ የሹመታቸው ቀን ያደረጉትን ንግግርና ከአራት አመታት በሁዋላ በቅርቡ ለፓርላማ የደረጉትን ንግግር ማነጻጸር ብቻ ይበቃል።  በፓርላማው ንግግራቸው ራሳቸውን እንደ ብሄር ተወካይ አድርገው ሲያቀርቡ ነበር። በሌላው በኩል ፓርቲያችን ከደምና ከአጥንት ቆጠራ ወጥቶ ፖለቲካዊ ውህደት አድርጓል ሲሉ ነበር። ከሁሉ በላይ በዚህ ንግግራቸው የምናየው ነገር ለውጡ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ወደ ብሄራቸው ለመደበቅ ሲጥሩ ታይተዋል። ይሄ አካሄድ የብዙ ስልጣን ወዳድ የአፍሪካ መሪዎች ክፉ ዘዴ ነው። ታላቋን ሶማሊያን እገነባለሁ ይሉ የነበሩት ዚያድባሬ ህዝባዊ ቅቡልነታቸው እየወረደ ሲሄድ መጨረሻ መደበቂያ ለማድረግ የፈለጉት ጎሳቸውን ነበር። ይህ የዚያድባሬ አካሄድ በሶማሊያ ውስጥ የነበረውን አንድ ብሄር በጎሳ ከፋፍሎ አፋጀ። እስካሁንም ዳፋው ሶማሊያን እያንገላታት ነው። ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ሲናገር ዶክተር አብይ በዚህ የፓርላማ ንግግር ላይ ያሳዩት ነገር ብሄርተኛነታቸውን ነው ሲል እያዘነ ተችቷል።  ታዲያ በዚህ ወቅት አኚህ መሪና ፓርቲያቸው ዝም ብለው ይቀጥሉ ብሎ መፍረድ በውነት በሃገር ህልውና ላይ መፍረድ ነውና ወደ ሽግግር በመግባትና ነገሮችን ማርገብ ተገቢ ነው።     

                          

3.   የለሂቅ ክፍፍል በመቀነስ ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት

 

ሌላው የሽግግር መንግስት ለመመስረት ግድ የሚያሰኘው ነገር የሃገራችን የለሂቃን ክፍፍል በየጊዜው እየከፋ ስለሚሄድ ነው። በዶክተር አብይ አመራር ጊዚያት ሁሉ የብሄር ለሂቃን አንድነት የሚመጣው በጥላቻ ላይ በመመርኮዝ ነው። ህወሃትን ለመደቆስ ሲባል ብዙ የብሄር ለሂቃን ፍቅር ይይዛሉ። ጦርነቱ ጋብ ሲል እርስ በእርስ ይናቆራሉ። ህውሃት ራሱ ጓድነት የሚመሰርተው በጋራ የሚጠላው ቡድን ሲያገኝ ነው። በአጠቃላይ በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የለሂቃኑ ወዳጅነት የጋራ ጠላትን ለማብሸቅ ሲባል እንጂ በመሰረታዊነት በሃገር ጉዳይ ላይ በሃገር ልጅነትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ህብረት አለመሆኑ የዚህን ዘመን የለሂቃን ፍቅር ልዩ ያደርገዋል። ይህ አይነት የለሂቅ መቀናጀት ሃገር ያፈርሳል። ይልቁን በአንድ ሃገር ልጅነት ላይ የተመሰረተ ለሃገር አሳቢ በመሆን የሚመጣ አንድነት ላይ መስራት ያስፈልጋል። የለሂቁ ክፍፍል ጊዜና ሁኔታ እያየ እዚያና እዚያ ሲላተም ስለ ሽግግር ማሰብ ተገቢና ጥበብ ነው። በዚህ ጊዜ ሃገራችን ማሰብ ያለባት ይህንን ፋክሽን ለማጥበብ ጠንክሮ መስራት ነው። የለሂቅ ክፍፍል ያለበት ሃገር ከእርስ በርስ ጦርነት ሊያርፍ አይችልም። የለሂቅ ክፍፍል ካለ የቱንም ያህል ሃብት ቢኖረንም እንኳን ሰላም ስለምናጣ አይጠቅመንም።

 

4.   በሃገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት ለማምጣት

 

አሁን ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚያሰክነው የፖለቲካ ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ችግሩ ፖለቲካዊ ነውና ፖለቲካዊ መላ ያስፈልጋል።  የፖለቲካ ለውጥ ሳይደረግ ዝም ብሎ ዛሬም ዶክተር አብይ ያሻግራሉ እያሉ በሃገር ላይ መፍረድ በእውነት ሃገርን ከአንድ ከባድ ጉዳት ወደ ሌላ ከባድ ጉዳት ያስገባል። ስለሆነም አሁን ያሉ የፖለቲካ ትኩሳቶች ሁሉ ረገብ እንዲሉ ሃገሪቱ ለውጥ ውስጥ መግባት አለባት ። ዶክተር አብይ ልክ አቶ ሃይለማርያም እንዳደረጉት ዘወር ይበሉና የሽግግር መንግስት ሃስብ ይነሳ።  ብልጽግ ና ተለውጫለሁ ሲል የመሪ ለውጥ ሳያደርግ አቶ ሃይለማርያምን እንደያዘ ቢቀጥል ድጋፍ አያገኝም ነበር። የአቶ ሃይለማርያም ቅቡልነት ወድቆ ስለነበር ማለት ነው። አሁንም ቢሆን ይህ ፓርቲ ቅቡልነታቸው የወደቀውን ዶክተር አብይን አውርዶ ለሽግግር ታጥቦና ጽድቶ መነሳት አለበት።

 

 

5.   ለብሄራዊ መግባባት

 

ከፍ ሲል እንዳነሳነው በቅርቡ የብሄራዊ መግባባት ኮሚሽን ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ ይህ ኮሚሽን በአንድ ፓርቲ ዝንባሌ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ዋና ዋና አጀንዳዎችን አንስቶ ለውይይት ያቀርባል ማለት አይቻልም። ገና ከጅምሩ እንደምናየው ግልጽ የሆኑ ብሄራዊ አጀንዳዎች እያሉ እነሱን እያድበሰበሱ አጀንዳ ከህዝብ ነው የምንቀበለው አካሄዳችን ከታች ወደ ላይ ነው ይላሉ። ይህ መርህ ላይ ላዩን ሲታይ ትክክል የሚመስል ዴሞክራቲክ የሚመስል ስለሆነ ብዙዎችን ዝም ያሰኛል። እውነቱ ግን ይህ አይደለም። ይህንን ትክክል የሚመስል ነገር ግን የተሳሳተ አካሄድ ይዘው ዋና አጀንዳ እያደበዘዙ፣ ለዶክተር አብይ የስልጣን ቀናት መጨመር የሚጨነቁ አይነት ናቸው።

 

የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ሆኖ ነገር ግን በመድብለ ፓርቲ ስርዐት ጊዜ ያልተለመዱ የስርዐት ግጭቶችን ለሂቂ ቁጭ ብሎ በፍጥነት እንዲወያይ መደረግ ነበረበት ዞሮ ዞሮ የሚመጡ ሃሳቦች ወደ ህገ መንግስት ሲቀየሩ አጽዳቂው ህዝብ ነው። ከውይይቶቹ ጎን ለጎን ህዝቡ የሚሳተፍበትን መድረክ እያዘጋጁ እንደ መሄድ ነገሮችን ሲያደበዝዙ ይታያል። ስለሆነም ይህ ኮሚሽን እንደ ሌሎቹ እድሜ ያለው አይመስልም። ከሁሉም በላይ ምርጫ አጭበርብሮ ቁጭ ባለና  በአንድ ፓርቲ ስር ሙሉ በሙሉ በወደቀ ፓርላማ ስር ሆኖ ሃቀኛነት በሃገራችን አይቻልምና ይህ አካሄድ ችግር ፈቺ አይደለም። ስለሆነም ነው የተውጣጣ የሽግግር መንግስት መስርቶ በዚያ ስር ልዩ የምክክር ኮሚሽን ይሁን ኮሚቴ አቋቁሞ መመካከር የሚያስፈልገው። ለተሳካ ብሄራዊ ምክክር በዚህ ሰዐት የሚያስፈልገው የሽግግር መንግስት መመስረት ነው።

 

6.   ለምርጫ የሰከነ ጊዜ ለማግኘትና የጸዳ ምርጫ ለማድረግ

     ምርጫ አንድ የሽግግር ምዕራፍ ነው። ነገር ግን ምርጫ የፖለቲካ ሴማ   

    ይጠይቃል። በአንድ ሃገር ውስጥ በብሄር ላይ ተደራጅቶ፣ በጂኦግራፊ ላይ   

      ተደራጅቶ፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ ተደራጅቶ፣ ደግሞ በየፊነው ሮጦ የጋራ ቤት

      ማቆም አይቻልም። እንዲህ አይነት ምርጫ መሳቂያ ነው። ምርጫ ለማድረግ   

      መጀመሪያ  የምርጫ መዳላድሎች መስተካከል አለባቸው። ፓርቲዎች በሃሳብ

       ተለያይተው ነገር  ግን በከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የተስማሙ መሆን   

       አለባቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ መግባባት ሳይኖር ምርጫ ማድረግ

       ልክ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ እንደሚባለው አይነት ችግር ነው የሚገጥመው።

       ከፍ ሲል ባነሳኋቸው  አጀንዳዎች ላይ መግባባት ከተያዘና ህገ መንግስት

       ከተሻሻለ በኋላ ምርጫ ማድረግ ሃገሪቱን በዴሞክራሲ እርሻ መም ውስጥ

        ይከታታል። ስለሆነም አሁን ሃገሪቱ ዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎቿን ለማረቅ

        የግድ የሽግግር መንግስት መመስረት አለባት ። ሃገራችን እዚህ የታሪክ

        መታጠፊያ ምእራፍ ላይ ትገናለች ።

 

 

 

 

 

              የሽግግር መንግስቱ ቅርጽ፣ ይዘትና ዋና ዋና ስራዎች

 

ከፍ ሲል እንዳነሳነው ይህ ወቅት የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚጠይቅ ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ምእራፍ ነው። ታዲያ ምን አይነት ቅርጽ ያለው የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት በሚለው ላይ መወያየት ያስፈልጋል። ከፍ ሲል እንዳነሳነው የተለያየ ቅርጽና ይዘት ያለቸው የሽግግር መንግስታት አይነቶች አሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ ሊሞከር የማይገባው ስልጣን ላይ ባለው ፓርቲ አማካኝነት እንሻገራለን የሚል የሽግግር አይነት ነው።  ከሁሉ በላይ የሃገራችን የሽግግር ጥያቄዎች ከባባድ በመሆናቸው በአንድ ፓርቲ አማካኝነት የተሳካ ሽግግር ማድረግ ስለማይቻል ነው። አሁን ሃገራችን ማዘንበል ያለባትና ወቅታዊ የሆነው የሽግግር መንግስት ጥያቄ ከሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች፣ ከሲቪክ ተቋማትና ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከምሁራን በተውጣጣ የሽግግር ምክር ቤት መመስረት ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ነው። ይህ ምክር ቤት የራሱን የስራ አስፈጻሚ መርጦ በምክክር የሚከተሉት ስራዎች ላይ ቢያተኩር ለተሳካ ሽግግር ይረዳናል።

 

1.      የሽግግር ጊዜ ቻርተር ማዘጋጀት፣ ደንቦችና እቅዶችን ማውጣት

 

2.  የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋምና በዚህ ኮሚሽን አማካኝነት የሃገሪቱን ዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎችን ማሻሻልና ይህንን የምክክር ሃሳብ ግብዐት አድርጎ የተሻለ ህገ መንግስት በጋራ ማርቀቅና በህዝብ ማጸደቅ

 

 

3.  የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚጸድቀው ህገ መንግስት መሰረት የፖለቲካ መስመሮቻቸውን አስተካክለው ለምርጫ እንዲዘጋጁ ማድረግ

 

4.  ታላቅ የምርጫ ድግስ መደገስና ሃገሪቱ ፍትሃዊና ነጻ የሆነ ምርጫ እንድታደርግ መደላድል መፍጠርና ምርጫ ማካሄድ

 

 

5.  የእርቅና የካሳ ኮሚሽን በማቋቋም በሃገሪቱ ውስጥ ብሄራዊ እርቅ እንዲሆን ሳያሰልስ ይሰራል

 

6.  የሽግግር መንግስቱ ከፍተኛ መሪዎች በዚህኛው ምርጫ ውስጥ እንዳይሳተፉ ማድረግና የመመረጥ መብታቸው ከዚህኛው ምርጫ በሁዋላ እንዲሆን ድንጋጌ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።

 

7.  በሽግግሩ ሂደት ላይ የህዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥና ግልጽነት ያለው አሰራር ማሳየት

 

 

8.   ተቋማት ማለትም ወታደሩ፣ ሲቪል ሰርቪሱ፣ ጤናው፣ ትምህርቱ ሁሉም ተቋማት ገለልተኛ በመሆን ለሽግግሩ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የሽግግር መንግስቱም ተቋማቱ በገለልተኝነት ስራቸውን እንዲሰሩ አመራር መስጠት።

 

 

 

 

 

 

          የሽግግር መንግስቱ ስጋቶች

 

 

1.      የውጭ ስጋቶች

 

የሽግግር መንግስት ሲቋቋም የውጭ ጣልቃገብነት እንዳይኖርና ሽግግሩ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን አለመረጋጋት የሚሹ ሃይሎች ሃገሪቱ የተሻለ ሽግግር እንድታደርግ አይሹም። ስለሆነም ይህንን ወቅት ተጠቅመው ሽግግሩን እንዳይጎዱት የሽግግር መንግስቱ ጠንቃቃና ንቁ መሆን አለበት ።  የሃገርን ብሄራዊ ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች በዚህ ንፋስ ውስጥ ገብቶ እንዳይጎዳን ከብሄራዊ ደህንነት ክፍሉ ጋር ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ካላት ስትራተጂካዊ አቀማመጥና ታሪካዊ አመጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች ያሉባት ሃገር ናት ። ከኤደን ባህረ ሰላጤ ዝንባሌዎች አንስቶ የውሃቢዝም መስፋፋት የሚሹ አሸባሪዎች ሁል ጊዜ ኢትዮጵያ የረጋ መንግስት እንዲኖራት አይሹም። የሽግግር መንግስት መመስረትና የፖለቲካ ለውጥ ማድረግ የሚፈጥራቸውን አንዳንድ ክፍተቶች ተጠቅመው የውጭ ሃይላት ሽግግሩን ለማኮላሸት ስለሚሰሩ ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ስለሆነም ወታደሩ ቀድሞ ከነበረው ንቃት ጨምሮ ዳር ድንበሩን መጠበቅ፣ ፖሊሲ ቀድሞ ከነበረው ንቃት ጨምሮ ወንጀል መከላከል፣ የጸጥታ ሃይሉ በንቃት መስራት ያስፈልጋቸዋል። ከሁሉ በላይ  አንዱ የሽግግር መንግስቱ ስራ ይህንን የውጪ ስጋት መተንተንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ነው።

 

2.   የውስጥ ስጋቶች

 

የሃገሪቱ የሽግግር ዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎችን የሚነካና የሚከልስ ስለሆነ በሃሳብ ታግለው ማሸነፍ የማይችሉ ሃይሎችና በተለይም የብሄር ኢንተርፕሩነሮች ሽግግሩን ለማደናቀፍ ይሰሩ ይሆናል። ነገር ግን ህዝቡና መንግስት ታግለው ይህንን ሃይል በመመከትና በማጋለጥ ሽግግሩን ከውስጥ ጥቃት ማዳን ያስፈልጋል።

 

በአጠቃላይ ከውጭና ከውስጥ የሚነሱ ፍላጻዎችን በመመከት ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን የመስራት ሃላፊነት በሽግግር መንግስቱ መሪዎችና በሁላችን ትከሻ ላይ ወድቋል።

 

         የሽግግር መንግስቱ እድሜ

 

የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት በምንም አይነት ከሁለት አመት ያለፈ እድሜ አያስፈልገውም። ስለሆነም ሃያ አራት ወራት ወይም ሁለት አመታት ተሰጥተውት በነዚህ ጊዚያት ስራዎቹን አጠናቆ በህዝብ ለሚመረጥ መንግስት ስልጣኑን የማስረከብ ግዴታ አለበት ።

 

           ማጠቃለያ

ኢትዮጵያውያን ስለ ሽግግር መንግስት ስናስብ ተስፋ መቁረጥና መፍራት የለብንም። እውነት ነው ኢትዮጵያ ሃቀኛ ሽግግር አይታ አታውቅም። ከደርጉ ጀምሮ ብንቆጥር ወደ አምስት የሚጠጉ የሽግግር ጊዚያት መክነውብናል። ይሁን እንጂ ወድቀን እየተነሳን የተሻለ ሽግግር አይተን ወደ ዴሞክራሲና ልማት ለመዘርጋት የምንታክት ዝንጉ መሆን የለብንም። ብዙ ሃገራት በዚህ ህይወት ውስጥ አልፈው ነው የተሻለ ስርዐት ፈጥረው በረጋ ሃገረ መንግስት ስር የሚኖሩት ። በመሆኑም አሁንም የሽግግር መንግስት ለማቋቋም መታገል አለብን።

ሃገራችን ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ትቀጥል ማለት ምን አልባትም የመንግስት መፍረስን ሊያስከትል ይችላል። ይህ አካሄድ ሃገሪቱን ልክ እንደ ሶማሊያ ሊያደርግ የሚችል አዝማሚያም አለው። በዚህ ሰዐት በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት፣ የሰላም እጦትና ጦርነት፣ ጥላቻና መተማመን እጦት ባለፉት አራት አመታት ሃገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ እየመሩዋት ስለሆነ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ አደጋ ነው። በብዙ ሃገራት የሽግግር መንግስት የሚቋቋመው ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በጊዜው የተሻሉ እርምጃዎችን ወስዶ ማስተካከል ሳይችል ሲቀር በወታደር ወይም በህዝብ አመጽ ገዢው መንግስት በሃይል ሲወገድ ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ መንግስት ይህንን የመወገጃ ጊዜ መጠበቅ የለበትም።

ብልጽግና ለሃገር ባለውለታ ይሆን ዘንድ እና ራሱንም ያተርፍ ዘንድ አሁን ስልጣን ላይ እያለ የሽግግር መንግስት ሃሳቡን ቢቀበል ትልቅነት ነው። በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲያርፉ ተደርጎ ከዚያም የሽግግር መንግስት ምስረታው እንዲሳለጥ ብልጽግና ቢሰራ በዚህ ውለታው የሽግግር መንግስቱ በሚያዘጋጀው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ላይ ትልቅ ነጥብ ይዞ ይገባል። ከሁሉ በላይ አብዮት ተነስቶ ይህንን ፓርቲ ጠርጎ ሳያስወግደውና አብዮታዊ የሽግግር መንግስት ሳይመጣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ለመፍጠር ዛሬ ስልጣን ላይ እያለ ይህ መንግስት ቢሰራ ትልቅ ነገር ነው።

 በሌላ በኩል ፓርቲዎች ይህንን ሃስብ መግፋትና ህዝቡን ለዚህ ጉድይ ማታገል አለባቸው። በአሁኑ አስተዳደር ጥቂት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚንስትሮች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ግለሰቦች ብልጽግና ካወጣው የፓርቲ ማኒፌስቶ ዝንፍ እንዳይሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነው የሚያገለግሉት ። ይህ አካሄድ አብሮ መስራትንና ሽግግርን አያሳልጥም። ሽግግር መንግስት ሲቋቋም የሽግግሩን ሮድ ማፕ በጋራ ሰርተው ከዚያም በፖሊሲ ተወዳድረው መንግስት የሚመሰረትበን ወይም ጣምራ መንግስት የሚመሰረትበን ሁኔታ ያመቻቻል።

ስለዚህ ሃገራችን ወደ ሽግግር መንግስት ምስረታ አሁኑኑ ማቅናት አለባት ። ግፊቶች ከሁሉም አቅጣጫ መምጣት አለባቸው። ይህንን ሳናደርግ በዋልን ባደርን ቁጥር ችግሮች አየተከመሩ ሄደው ሃገራችን የከፋ ችግር ላይ ልትወድቅ ትችላለች ። ስለዚህ ሁላችንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ዘንድ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከስልጣን ይነሱ ዘንድ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል። የዘር ማጥፋት ወንጀል መርዶ በሰማን ጊዜ በቃ! እንላለን። ነገ ደግሞ እንዲሁ ሌላ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስንሰማ በቃ እንላለን። አሁንም ሌላ የዘር ማጥፋት ወንጀል መርዶ ስንሰማ በቃ! እንላለን። በዚህ ሰዐት ኢትዮጵያ ውስጥ በቃ! የሚለው መፈክር ትርጉም አጥቷል። በቃ የሚለው ቃል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንጂ የዘወትር መፈክር አይደለም። ሃገራችን በማያባራ ስደትና መፈናቀል፣ ረሃብና የኑሮ ውድነት፣ በሰላም ማጣትና በጦርነት ስትታመስ በቃ! የሚለው መፈክር አይሰራም። አሁን የሚፈለገው መፈክር ዶክተር አብይ ከስልጣን ይነሱና ባስቸኳይ የሽግግር መንግስት ይቋቋም! የሚል መሆን አለበት። ይህ ሲሆን መዋቅራዊ ችግሮቻችንንና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችንን ለመፍታት ሌላ እድል እንፈጥራለን።

 

 ዶክተር አብይ ስልጣን ይልቀቁ! የሽግግር መንግስት ይቋቋም!

 

          እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ ይባርክ!

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...