ድባብ መናፈሻ ውስጥ ከ አንድ ጓደኛዬ ጋር ወግ ይዘናል::ለዛ ባላቸው ቀልዶች እያዋዛ ቁምነገር
ስለሚያቀብለኝ ከዚህ ሰው ጋር ጊዜ መውሰዱ ያስደስተኝ ነበር:: ታዲያ በዚህ ቀን ስለሆነ ስለሆነ ነገር
ስናወጋ አንድ ከልብ የሚቀር ታሪክ አጫወተኝ::በርግጥ ስለ ታሪኩ ርግጠኝነት አጥብቄ መጠየቅ
አልፈለኩም በውስጡ ያለው የተዛምዶ ትምህርት አሳስቶኝ ነበርና::
ታሪኩ እንዲህ ነው::አንድ የእግር ኳስ ዳኛ ሁለት ተፎካካሪ ቡድኖችን በመሃል ዳኝነት ይመራ
ይዟል::በጨዋታው መሃል የአንደኛው ቡድን አጥቂዎች ወደ ተቃራኒው ቡድን የግብ ክልል አካባቢ
ደረሱ::በመሃልም የተቃራኒው ቡድን ተከላካይ ኳሷን ከአጥቂው ለማስጣል ይንሸራተት እና ኳሷን
ይነጥቃል::መነጠቁን ያወቀው አጥቂ ተጠልፎ እንደወደቀ አስመስሎ ይወድቃል::ይንፈራፈራል::ዳኛው
ምንም እንዳልተጠለፈ በሚገባ ቢያይም ባልገባው ድንገተኛ ስሜት ፊሽካ አጮኸ::ተጣድፎም ፍጹም
ቅጣት ምት እንዲመቱ አደረገ::ያ ያጭበረበረው አጥቂ ቅጣት ምቱን መታና ግብ ተቆጠረ::በ አጭበርባሪው
ወገን ሆታ በ ተቃራኒው ወገን አዘን ረበበ::
በደል የደረሰባቸው ተጫዋቾች ጥቂት የተሟገቱ ቢሆንም ዳኛው ስለወሰነ ምንም ማድረግ አልቻሉም::
ጨዋታው ቀጠለ::የመሃል ዳኛው ባላወቀው ስሜት የፈጸመው በደል ከወዲያ ወዲህ እየሮጠም
አለቀቀውም::ጥፋቱ ህሊናውን እየከሰሰው ነው::
አሁንም ኳስ በነዚያ ግብ በገባባቸው ቡድኖች የግብ ክልል አካባቢ ትገኛለች:: አንድ ሁለት አንድ ሁለት
ተቀባበሉ::ተከላካይ በቅብብሎሹ መሃል ዘሎ ኳስ አጨነገፈ::ይሁን እንጂ ማጭበርበር የለመዱት እና
የዳኛውን አለመረጋጋት ያዩት አጥቂዎች ባንዴ እጃቸውን አወጡ::ማኖ......::የመጀመሪያው ስህተት
አይምሮውን እየወቀረው ያለው ዳኛ አልተረጋጋም ሌላ ስህተት ሊደግም ነው::ፊሽካ በረጅሙ አሰማና
የሁለተኛ ቅጣት ምት እንዲመቱ አዘዘ::ለሁለተኛ ጊዜ በደል የደረሰባቸው ተጫዋቾች ዳኛውን ከበው
ጠየቁት::ዳኛው የሁለተኛው ውሳኔውም ስህተት እንደነበር ወዲያው ፊሽካ ካሰማ በሁዋላ አውቋል ይሁን
እንጂ አንዴ ፊሽካ አስምቻለሁ ብሎ በውሳኔው ጸና::ቅጣት ምቱ ተመታ:: ሁለተኛ ግብ ተቆጠረ::
ዳኛው በመደናገር የፈጸማቸው ስህተቶች አእምሮውን ይጠዘጥዙት ይዘዋል::በደል የተፈጸመባቸው
ተጫዋቾች ተስፋ ባለመቁረጥ ደፋ ቀና ማለታቸውን ሲያይ አዘነ መሰል::ሰአቱ ገፋ::በ አግቢዎቹ መንደር
ሆታ ና ድል ሲዘፈን በተበዳዮች ደጋፊዎች ዘንድ ተስፋ መነመነች::ለጨዋታው የተመደበው ጊዜ ሊያልቅ
ነው::በትልቁ ስክሪን ላይ የቀሩት ሁለት ደቂቃዎች ብቻ መሆናቸው እንደታየ ያልተለመደ የፊሽካ ድምጽ
ዳኛው አሰማ::በ አግቢዎች ዘንድ ለቅጽበት ዝላይ ሆነ የተበዳይ ደጋፊዎች ደግሞ "ሰአት ሰአት ሰአት"
ጩኸት ሆነ::ይህ ሁሉ ለቅጽበት ነበር:: ዻኛው ልክ በእጅ መስታወት ፊታችንን እንደምናይ ቀይ ካርድ
አውጥቶ ለራሱ ያያል::ለጥቂት ሰከንዶች ቀይ ካርዱን ለራሱ ካሳየ በሁዋላ::ሜዳውን ሰንጥቆ ወጣ::ግራ
መጋባት በስቴዲየሙ ዙሪያ ደበበ:: አራጋቢዎች ሮጠው ተጠጉት::ለሁለቱም ቀይ ካርዱን አሻራቸው::ግራ
መጋባቱ በስቴድየሙ መላ::
ብዙ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ዳኛው ወዳመራበት ተሯሯጡ::ከ ጥቂት ግራመጋባት በሁዋላ::በድምጽ
ማጉያ እንዲህ ተለፈፈ::
“ዻኛው ባልተለመደ ሁኔታ ለራሳቸው እና ለ አራጋቢዎቻቸው ቀይ ካርድ አሳይተው ጨዋታውን
አቋርጠዋል::ተመልካቾች በተፈጠረው ሁኔታ ይቅርታ እየጠየቅን የዛሬው ጨዋታ በዚሁ ተቋርጧል ስለዚህ
ሰሞኑን የፌደረሽኑ ወሳኔ ስለሚገለጽ በሚዲያ እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጠይቃለን::”ተመልካች እርስ
በርሱ ስለተፈጠረው አስገራሚ ነገር ያወጋል::ግማሹ ዳኛውን ያደንቃል::ግማሹ ይገረማል::
ከቀን በሁዋላ ፌደረሽኑ ጨዋታው እንዲደገም እና ሌላ ዳኛ ጨዋታውን እንዲመራው በመወሰኑ እነዚያ
ተቃራኒ ቡድኖች ፍልሚያ ገቡ::ጥሩ ተጫውተው እነዚያ በደል የተፈጸመባቸው ተጫዋቾች ሶስት ለባዶ
ረተው ገቡ::ያ ለራሱ እና ለ አራጋቢዎቹ ቀይ የሰጠው ዳኛ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት እንዲህ አለ::
"የወሰድኩት ርምጃ ትክክል ነበር::ሃጥያቴም ታጠበልኝ::"
ይሄ ጓደኛዬ ይህን ካጫወተኝ በሁዋላ በረጅሙ ተንፍሶ እንዴው በሁሉም መስክ እንዲህ ያሉ ጀግኖች
ቢኖሩ እንዴት መልካም ነበር? ብሎ አስደመመኝ::
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com__
No comments:
Post a Comment