Friday, June 29, 2012

በግለሰቦች መብት ያለም የመጨረሻዋ አገር

ባለፈው ጊዜ ሌጋተም የተባለው ድርጅት 110 አገሮችን የብልጽግና ደረጃ ሲያጠና ሰንብቶ ባወጣው ሪፖርት ላይ አጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያ እንደተለመደው ወደ መጨረሻው ሆና 108 ወጥታለች:: እንዲህ አይነቱ የመጨረሻ አካባቢ ውጤት የተለመደ በመሆኑ እምብዛም አልተገረምን:: ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ታዲያ ካሉት የብልጽግና መለኪያ ተለዋዋጮች(variables) መካከል በጣም አስፈለጊ በሆነው የግለሰቦች መብት(personal freedom) 110 110 የመሆኑዋ ነገር የበለጠ ትኩረቴን ስቦኝ ነው::የግለሰቦች መብት ጉዳይ የሃገር ዋልታና ማገር ሆኖ በዚህ ቫርያብል ያለም መጨረሻ የሆነችው ኢትዮጵያ በየአመቱ ደብል ዲጂት ታድጋለች እያሉ የመቀለዳቸው ነገር እንደገና እንዲገርመን ያደርጋል:: በነገራችን ላይ ሌሎች በጥናቱ ያልታቀፉ ሃገሮች ቢካተቱም የመጨረሻውን ደረጃዋን መያዙዋ የሚቀር አልነበረም::በዚህች አጭር ጽሁፍ ጥቂት የዚህን የመጨረሻ ደረጃ እንድምታ አንድ ሁለት እያልን ለቸኮለ አንባቢ በሚሆን አይነት በአጭሩ ለመግለጽ እንሞክር::

በግለሰቦች ነጻነት ያለም መጨረሻ መሆናችን የሚያሳየው፤-
፩) የአምባገነንነቱ ደረጃ ጥግ መርገጡን የአምባገነንነት አንዱ መገለጫ ግለሰቦችን አፍኖ በመያዝ ደረጃው ይገለጻል:: እንግዲህ ታዲያ አገራችን በግለሰቦች መብት ያለም መጨረሻ ከሆነች ገዢው ህወሃት ኢህ ያለም የመጨረሻ አምባገነን መንግስት ነው ማለት ነው:: በሌሎች ጥናት እንደሚታየው ኢትዮጵያውያን አገር ጥለው ለመጥፋት ባላቸው ፍላጎት ክአለም ክፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሶ በጣም ድሃ ከሚባሉት ከነ ኒጀር እና ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ህዝቦች ሁሉ በላይ ኢትዮጵያዊያን አገር ጥለው የመጥፋት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ሆኑዋል። ወገኖች ዛሬ በየበረሃው ባስቃቂ ሁኔታ የሚያልቁበት አንዱ ትለቁ መነሻ የነጻነት ማጣት ነው። በሌላ አገላላጽ ግለሰቦች ባላቸው ችሎታ ተሰማርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚችሉበት እድል( opportunity) ያለም መጨረሻ ደረጃ ላይ ነው ማለት ነው። ይህም ያቶ መለስ አስተዳደር ያምባገነንነት ደረጃ አድጎ አድጎ የደረሰበትን ደረጃ እንድንረዳ ያደርጋል።

፪) ለብርቱካናማው አብዮት የማእዘኑ ድንጋይ በምን አይነት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መሆኑን
በሃገራችን ውስጥ በብርቱካን አብዮት ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው ብለው ለሚያምኑ ወገኖች ይህ ጥናት መልክት ይዙዋል። የግለሰቦች መብት በከፍተኛ ደረጃ ከሚባለው አልፎ ባለም መጨረሻ ደረጃ ባለች አገር እንዼት ተደራጅቶ መታገል እንደሚቻል እንደገና መልስ ሊሰጡበት ይገባል።
የምታስታውሱ ከሆነ የ1997 ምርጫ እየተጭበረበረ በነበረበት ሰሞን አቶ መለስ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው በብርቱካናማው አብዮት ሲቀልዱ ቃል በቃል ባላስቀምጠውም “ተቃዋሚዎች የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እየጠሩ…”.አይነት ተናግረው ያፌዙበት ትግል ነው። ዛሬ ደግሞ እያደር አምባገነንነቱ አድጎ የግለሰቦች መብት ጉዳይ አዘቅት ወድቁዋል። ይህ ማለትም የሰኪዩሪቲው ጉዳይ ከሚገባው በላይ ሆኑዋል አይወራም ማለት ነው።
ግለሰቦች መውጣት መግባታቸውን ሁሉ በፍርሃት ያያሉ ጉዋዳኝነት መስርቶ የሆድ የሆድ ለማውራት ይፈራሉ ስልኮቻቸው ኢሜይላቸው ፖስታቸው ሁሉ በሰላዮች ይፈተሻል ታድያ በንዲህ አይነት አገር የሚኖሩ ዜጎችን የፖለቲካ ጽ/ቤት ከፍቶ በግልጽ ለመደራጅት እንዴት እንደሚቻል ዛሬስ እንደገና እንዲያስቡ የሚያደርግ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ተደርሱዋል ማለት ነው።
    
፫) የቡድን መብት አብሮ መረገጡን ያሳያል
ቡድን የግለሰቦች ውጤት ነው። ያለ ግለሰቦች ርካታ ቡድን ሊረካ አይችልም።አንዱ ግለሰቦችን እንዳይረኩ የሚያደርጋቸው ነገር ደግሞ ዘርና ቁዋንቁዋ ሲፖተለክ ነው። ሕወሃት ኢ ህ አ ዴ ግ ስልጣን ለመያዝም ከያዘም በሁዋላ የሚያዘምረው ነገር የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጉዳይ ነው። የብሔሮችን መብት አስከብረናል የሚባለው ጨዋታ በተግባር የሚፈተሽበት ቦታ በግለሰቦች መብት ደረጃ ነው። ግለሰቦችን እየረመረመ ስለ ቡድን ቢያወራ ከተግባር የራቀ ማምታቻ ፕሮፖጋንዳ ነው የሚሆነው።
የዼሞክራሲ ትልቁ መሰረት ግለሰብ ሲሆን በርግጥ ቡድኖችን እንደየ ባህርያቸው መንከባከብም አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው። በዚህ ረገድ ወያኔ ለውጥ ማምጣቱ ቀርቶበት ቡድኖችን ለገዛ ፖለቲካው ተጫውቶባቸዋል።
፬) ለተቃዋሚ ሃይሎች ህብረት ማጠናከሪያ ጥሪም አለው
    የግለሰቦች መብት ሲባል የሁሉም ዜጎች መብት ማለት ነው። ጥቂት በስልጣን ላይ ያሉና ንክኪ ያላቸውን ከቁጥር እናውጣና ሌላው አማራ ኦሮሞ ትግሬ ጉራጌ ወዘተ.ተጠቂ መሆናቸውን ነው። የግለሰብ መት ጉዳይ የሁሉም ብሄሮች ጥያቄ ነው። ዜጋ የሆነ ሁሉ የዜግነት መብቱን ጠይቆ ነው ወደ ሌሎች ጥያቄዎች የሚዘረጋው። ትግሉ የጋራ ባህርይ እንዲኖረው ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ይሄ ነው።
፭) ግለሰቦች ለትግሉ ሃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅም ነው
    የግለሰቦች መብት ጉዳይ በሃገር ደህንነት ስም ታጅሎ የመጣ አይደለም። በእያንዳንዳችን ቤት የመጣ ወደዚህች አለም መጥተን ኢትዮጵያ በምታል አገር ተፈጥረን የሚገባንን የዜግነት መብት ስናጣ ሃላፊነት መውሰድ የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል። ጥያቄው የድርጅት ወይም የቡድን ሳይሆን የግለሰብ ነጻነት ጉዳይ በመሆኑ ነው ግለሰቦች ሃላፊነት ሊወስዱበት ይገባል እንድንል የሚያደርገን።
               
                ቸር ይግጠመን ደሞ
                     ገለታው ዘለቀ
              geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...