Tuesday, July 9, 2013

ሁለቱ ማንነቶቻችን ፉክክር ውስጥ ባይገቡ? (Article)

ገለታው ዘለቀ 

ባለፈው ጊዜ  ኣንድ ወንድማችን በኣልጃዚራ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ “እኔ በመጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ…” በማለታቸው ኣንዳንድ ነቀፌታዎችን እየሰማንና እያነበበን ነው። ነገሩ ግን ኣዲስ ኣይደለም። በኢትዮያ ውስጥ የባህል ቡድን ፖለቲካ ከተጀመረ ጀምሮ ኣንዳንድ ወገኖች በስሜትና በእልህ ይህን ሲግልጹት ይታያል። እንዴውም ኣሁን ትንሽ ረገብ ያለ ይመስላል።የሆነ ጊዜ በጣም ጦፎ ነበር።
 የዚህች ጽሁፍ መነሻ ታዲያ በፍጹም ግለሰቡን በመንቀፍ ወይም የዚህን ኣመለካከት ኣቀንቃኞች ስሜት ለማናናቅ ኣይደለም። ይልቁን በወንድማማችነት ስሜት በመሰረተ ሃሳቡ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ነበር።ሃስባችንን ፍፉ ለማድረግ ይሄን ማንነት(Identity) የሚባለውን ነገር በሁለት ከፍለን ለማየት እንሞክራለን። ኣንደኛው ማንነት ማህበረሰባዊ የሆነ ማንነታችን ሲሆን ሁለተኛው ፖለቲካዊ ቅርጽ ያለው ማንነት ነው። በንጹህ ሶሲዩሎጂ እይታ(perspective) ማንነት ሲነሳ ኣንድ ሰው እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ኣማራ ነኝ፣ እኔ ትግራይ ነኝ ወዘተ. ቢል ተፈጥሮኣዊ ነው። ይህን በማለቱ ሊኮራ እንጂ ሊያፍር፣ ሊሸማቀቅ ኣይገባውም። እንዴውም በዚህ መንግስት ክፍፍል መሰረት ኣናሳ ብሄርና ገዛፋ ብሄር የሚባል ነገር ኣለ። ከዚህ በፊት በጻፍኳት ኣንዲት ብጣቂ ኣርቲክል ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ባህላዊ ቡድን ኣናሳ ወይም ገዛፋ ኣይባልም። ቡድንን ቡድን የሚያሰኘው ቋንቋውና ባህሉ ታሪኩ በመሆኑና የማንም ባህል ከማንም ስለማይበልጥ፣ የማንም ቋንቋ ከማንም ስለማያንስና ስለማይበልጥ ቡድኖች ትልቅ ትንሽ ሊባሉ ኣይገባም። ሁሉም እኩል ናቸው። ስለሆነም ሰው በቡድኑ ቢገለጽ መልካም እንጂ ክፋት ስለሌለው ኮንሶ ነኝ፣ ሃመር ወዘተ. ማለት ሊያሳፍር ኣይገባም።
 ኣንድ ሰው እኔ ኦሮሞ ነኝ ሲል ሊኖረው የሚገባው ትርጉም  የራሱ የሆነ ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ታሪክም ያለው ቡድን ውስጥ ተወልጄ ያደኩ የዚያ ማህበረሰብ ኣባል ነኝ ማለት ነው። ከዚህ በላይ ለጥጦ ማርቀቅ ሌላ ኣጀንዳ ሲኖር ነው። ይህን ማንነት መግለጽ ደሞ ሃጢያትም ኣይደለም እንዴውም የሚበረታታና ደስ የሚያሰኝ ነው ብለናል። ይህ ማለት ግን ከደም ሃረግ ጋር ሊደባለቅ ኣይችልም። ምክንያቱም የደም ሃረግ ሁል ጊዜ በኣንድ ባህላዊ ቡድን ውስጥ ኣይገኝም። የደም ሃረግ ወደላይና ወደ ጎን እስከ ተወሰነ ደረጃ እየተለጠጠ ሲሄድ እየሳሳ እየሳሳ ሄዶ መጨረሻ ላይ ይደበዝዛል። ኣያት ቅድም ኣያት ብሎ ከሰባት በላይ መሄድ ከባድ ነው። ወደጎንም ጥቂት ያጎት ልጅ ምናምን ብለን እናቆማለን። የሰሜን ኣካባቢ ህዝብ በጋብቻ ጊዜ እስከ ሰባት ይቆጥርና ከዚያ ካለፈ ጋብቻ ይፈቅዳል። ለምንድነው? የደም ሃረጉ ሳስቷል ወይም ኣይታይም ከሚል ነው መሰለኝ። ስለሆነም ራስን በባህል ቡድነኝነት መግለጽ ከደም ሃረግ ጋር የተገናኘ ነው ብሎ ማካበድ ከእውነት የራቀ ነው። የደም ሃረግን በጣም እንለጥጠው ካልን ኣዳምና ሄዋን ወይም ሉሲ ጋር ደርሰን ጥያቄያችን ሁሉ ኣፈር ይበላል። በሌላ በኩል በኣንድ የባህል ቡድን ለምሳሌ በጉራጌ ብዙ ጎሳዎችም ኣሉ። ስለዚህ የባህልን ቡድን መሰረት ኣድርገን ራሳችንን ስንገልጽ ከባህልና ከቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው የሚሆነው።ከዚህ የዘለለ ነገር የለውም ለማለት ነው።
ሁለተኛው ማንነታችን ፖለቲካዊ ቅርጽ ያለው ሲሆን ይህን ከላይ ያነሳነውን ንጹህ ማህበራዊ መገለጫ ፖለቲካዊ ይዘት እምዲኖረው ስናደርግ ኣደገኛ የሆነ ነገር ውስጥ ይከተናል። በኣሁኑ ሰኣት በኢትዮጵያ ውስጥ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ ትግራይ ነኝ ወዘተ ሲል ቶሎ ብልጭ የሚልብን ፖለቲካዊ ግፊት(motive) ኣለው ብለን ስላመንን ወይም የውነትም ስለሆነ ነው። ፖለቲካዊ ማንነት ማለት በኣንድ ፖለቲካዊ ውቅር፣ በጋራ ታሪክ፣ እሴትና መሬት የቆመን ማንነት ማለታችን ነው። ይህም በርግጥ ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ ማንነትና ከፍ ሲል ያነሳነው ሶሲዩ ካልቸራል ማንነት መደባለቅም ፍክክርም ውስጥ መግባት የለባቸውም።
ተፈጥሯቸው የተለያየ እንደመሆኑ በተለያየ መስመር ሁለቱም ኣንደኛ ናቸው። በመጀመሪያ እኔ ኦሮሞ ነኝ ካልን በርግጥ የሚከተል ነገር ኣለ ይህም ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ ችግር የሚመጣው የባህልና የቋንቋ ማንነታችንን ፖለቲካዊ ሸማ ስናለብሰው ነው። ሁለት መሽቀዳደም የማይገባቸውን ነገሮች ለማሸቀዳደም እንድንሞክርና ግራ እንድንጋባ ያደረገን በርግጥ የወቅቱ የጎሳ ፖለቲካ ድባብ ነው።
እንደዚህ የፖለቲካ ማንነታቸውና የባህል ቡድን ማንነታቸውን ኣደባልቀው የሚሄዱ ወይም ለማሽቀዳደም የሚሞክሩ ሌሂቃን ብዙ የሳቱት ነገር ኣለ። በመጀመሪያ ደረጃ እነደሚያስቡት ባህላዊ ቡድንን ኣንደኛ መገለጫ ካደረጉት ሁለተኛው መገለጫ ያው ኢትዮጵያዊነት መሆኑ ነው። የዚህ ማንነት ገለጻ ችግሩ 82ቱም ባህላዊ ቡድን ኢትዮጵያዊነትን ሁለተኛ ደረጃ መገለጫው ካደረገ የሚፈጠረው ነገር ኣንድም እጅግ በላላ ኣስተዳደር(confederation) ተስማምተን መተዳደር ወይም 82 ጎረቤታማ ሃገራት ሆነን እንድንቀመጥ ነው የሚያደርገን። ይህ ደሞ ለሁሉም ቡድኖች ህልውና ኣደጋ ነው።ለዚህ ነው ፌደራሊዝምና የ ባህል ቡድን ፖለቲካ  ኣብረው ለመሄድ ሲሞክሩ ከባድ ፈተና የሚገጥማቸው።  
የባህል ቡድናቸውን ፖለቲካዊ መገለጫቸው ያደረጉ ምሁራን ወደስልጣን ሲመጡ ያ በመጀመሪያ እኔ የዚህ ብሄር ኣባል ነኝ የሚለው መሪ መፎክራቸው ወደ ተግባር መዘርዘር ሲጀምር ኣድልዎና ጠባብነትን ያመጣል። ከዚያም በላይ ደሞ ከሌላው ቡድን ጋር ጎን ለጎን ሲቆሙ ለባህላዊ ቡድናቸው ተቆርቋሪ ይምሰሉ እንጂ በዚያው በባህል ቡድናቸውም ውስጥም ኣያርፉም። ራሱ ትምህርቱ ዝርዝር ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያደርጋቸው ከዚያው ባህል ቡድን ውስጥ ትናንሽ ቡድኖችን እየሰሩ ብዙ ማንነቶችን ይፈጥራሉ። ለዚህ ነው ኣጥባቂው ህወሃት ከሌላው ቡድን ጋር ሲቆም ለቡድኑ ተቆርቋሪ ይመስላል ብቻውን ሲሆን  ውስጡ ሲገባ ደሞ ኣንዴ ኣድዋ ኣንዴ ኣክሱም እያለ የክብ መኣት ሲሰራ ይታያል።
በመጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሰው ኢትዮጵያዊነቱን ሁለተኛ የፖለቲካ ማንነት መገለጫው ኣድርጎ ብዙ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማስተዳደር እድል ሲያገኝ በመጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ የሚለውን ወደ ተግባር መዘርዘር ሲጀምር የቡድኑን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ቅድሚያ ሰጥቶ እያሙዋላ ከዚያ በተራረፈው ሌላውን ሊያስተናግድ ይገፋዋል ማለት ነው። ለዚህ ነው የባህል ማንነት ጉዳይ ፖለቲካዊ ልብስ ሲሰፋለት ፍትህ ራቁቷን ትቀራለች ብለን እንድናስብ የሚያደርገን።
በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የማንነት መምታታት ሲመጣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው እንዳይፈርስ የፈሩትን ኣገር ወዳዶቹን ደሞ ወደ ሌላ ጥግ ሲወረውር ይታያል። እኔ በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከዚያ….. ብለው ብሄራቸውን ይጠራሉ። ይህ ማለት የባህል ቡድን ማንነታቸው ሁለተኛ ደረጃ ይኖረዋል ማለት ነው። ይህ እልህ የፈጠረው የመጀመሪያውን ኣገላለጽ በተቃራኒ ለመዋጋትና ለመከላከል የመጣ ስሜት ነው። ግን ከፍ ሲል እንዳልነው እነዚህ ማንነቶች ለየቅል ናቸው:: ውድድር ውስጥም ኣይገቡም። ሁለቱም በተለያየ ህግ በኣንደኝነት ልንንከባከባቸው ነው የሚገባው።
የራስን ባህላዊ ቡድን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ኣድርገው የሚነሱ ሰዎች መነሻቸው ኣንዱ በድሮው ጊዜ ተጽእኖ ተደርጎብናል፣ ስማችንን በግድ ቀይረናል፣ በባህላችን ኣፍረናል ወዘተ የሚሉ ቂሞች ናቸው። ርግጥ ነው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደል ተፈጽሙዋል።በርግጥ በዚህ መንግስት ከሚገባው በላይ የተራገበ ቢሆንም በደል ባራቱም ኣቅጣጫ ነበር። ግን ደሞ በመላው ኣለም ያለው የማህበረሰብ እድገት ታሪክ እንደሚያሳየን ብዙ ኣገሮችም በዚህ ኣይነት ህይወት እንዴውም በከፋ ሁኔታ ነው ያለፉት። ያኔ የነበረውን ኣስተዳደር ኣሁን በደረስንበት መረዳት ለመዳኘት መሞከሩም ሚዛን የጎደለው ይመስላል።
ከሁሉ በላይ ይህን ቂም እንዴት ነው የምንበቀለው የሚለውን መምከር ኣለብን። እንግዲህ ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ ኣልፋ እዚህ በኛ እጅ ደርሳለች። ታዲያ ያለፈውን ኣመጽና ግፍ ቆጥረን እንደገና እንበታተንና ትንሽ ኣይተነው ተመልሰን እንሰባሰብ ነው ነገሩ ወይስ ምንድነው?ወሰኑስ የትና የት ሊሆን ነው? ይልቅ ያን ታሪክ የምንበቀለው  የከሰሙ ባህሎች ካሉ እንዲያንሰራሩ በማደረግና በማደስ፣ ኣዳዲስ የማስመለስ(restoration) ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ነው። ስለ ድሮው ኣንስተን ብንጨቃጨቅ በዳይና ተበዳይ በህይወት በሌሉበት ብንወቃቀስ ዋጋ የለውም። ይልቅ ኣለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በእውቀት ጥሎን እየነጎደ ነውና ማስተዋል ኣለብን።
በሌላ በኩል ደሞ ቂም ብቻ ሳይሆን ኣንዱ ያስመረራቸው ጉዳይ  በኣሁኑ ሰኣት ያለው ኣድልዎና ግፍ ነው።እኚህ ኢንተርቪው የተደረገላቸው ወንድማችን በኣሁኑ ሰኣት መንግስት በኦሮሞው ላይ በተለይ ችግር እየፈጠረ ነው ኦሮሞን ለይቶ እያጠቃ ነው የሚል ገልጸዋል። ይሄ እውነት ነው። ግን ደሞ ሌላውም እንዲሁ ይሰቃያል። ዋናው ነገር ግን ይህ መንግስት ለምንድ ነው ቡድን እየለየ የሚያጠቃው? ካልን ዘረኛ ስለሆነ እኮ ነው። ለዚህ ኣይነቱ ግፍ ዘረኛ መሆን ኣይደለም ችግሩን የሚፈታው። ኣማራ ሲመታ ኣማራው ብቻውን መጮህ፣ ኦሮሞው ሲመታ ኦሮሞው ብቻውን መጮህ ከጀመረ ባንድም በሌላም መንገድ የዘረኛው ፖለቲካ ሰላባ መሆናችንን ያሳያል ከሁሉም በላይ ተግባራዊ መፍትሄ ለማምጣት ያስቸግራል።
ኢትዮጵያዊያን በዚህ በማንነት ፍልስፍና ስንዋኝ ኢፍትሃዊነት ትንፋሽ ኣግኝቶ ወገናችንን እያጠቃው ነው። ከዚህ በፊት በኣንዲት ኣጭር ኣርቲክል ለመግለጽ እንደሞካከርኩት መገንጠል ኣንድ ነጠላ ብሄር ሆኖ መገኘት ለፍትህና ለዴሞክራሲ መስፈን ምንም ዋስትና የለውም። ይልቅ በጋራ ታግለን ዴሞክራሲን ወደቤታችን እናምጣ። ያኔ ጥያቄዎቻችን ሁሉ ይፈታሉ።
ተፈጥሮኣዊ ማንነታችን ያለው ከጣታችን ኣሻራ ላይ ነው። ሌላውን ሁሉ ተምረን ነው ያገኘነውና ጉዳዩን ከማራገብ ይልቅ ኣብረን የፈረሰውን ቅጥር ለማደስ እንውጣ።
                                እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ !       

                                 geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...