ይህን ኣባባል ስንቀባበል የኖርነው ያለ ምክንያት ኣልነበረም። ሃገራችን ብዙህነቷ የሚገለጸው በ ቋንቋና በ ባህል ብቻ ሳይሆን በ ሃይማኖትም በመሆኑ ነው። ብሂሉ ተቻችለን መኖር እንዳለብን ቃል የምንገባበት፣ የሃይማኖት ነጻነታችን የ ግል ሆኖ ኣገራችን ግን የሁላችን መሆኑዋን የምናጸናበት ኪዳን፣ የ ኣንድነት ጉዟችን ደሞ ስንቅ ነበር።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ትልቅ ኣላማ የሚያናጋ ሁኔታ ሲፈጠር ይታያል። የሚያሳዝነው በሃገራችን ከተነሱ ሃይማኖታዊ ግጭቶች መካከል እጅግ ብዙዎቹ ፖለቲካዊ ይዘቶች ያሉዋቸው መሆኑ ነዉ ።
በመሰረቱ ፖለቲካና ሃይማኖት የሚጣሉ ባይሆኑም ኣላማቸው ግን ኣይገናኝም። ሃይማኖታዊ ተቋማት ከዚህ ኣለም ባሻገር ሌላ ኣለም ኣለ ወደዚያ ሄጄ ዘላለም እኖራለሁ የሚል ዋና ግብ ያነገቡ ሲሆን ፖለቲካ የዚህ ኣለም ጣጣ በመሆኑ ለየብቻ መሄድ ኣለባቸው።
ከሁሉ በላይ ግን መንግስት ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት መቆጠቡ የሚጠቅመው ራሱን ነው።የ ሃይማኖት ተቋማት በ ህብረተሰብ ህይወት ውስጥ ካላቸው የጎላ ጠቀሜታ መካከል ኣንዱ የፍትህ ስርዓቱን በመደገፉ ረገድ ያላቸው የጎላ ሚና ነው። ለምሳሌ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ስናይ ኣንድ ሰው ለ ምስክርነት ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ በ መጀመሪያ እውነት ለ መመስከሩ ቃል የሚገባው ህገ መንግስቱ ላይ እጁን ጭኖ ሳይሆን ክርስቲያን ከሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ሙስሊም ከሆነ በቁራን ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው ፍርድ ቤት ወይም የፍትህ ስርዓቱ ከ ሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ ቢሆንም ግን በነዚህ ተቋማት ላይ መደገፉን ነው።
እነዚህ የ ሃይማኖት ተቋማት ኣባሎቻቸውን የሚያስተምሯቸው እሴቶች ለምሳሌ፣ ኣትግደል፣ በሃሰት ኣትመስክር፣ ኣታዳላ፣ ግፍ ኣትስራ፣ ወዘተ. የፍትህ ስርዓቱ ምሶሶዎች ናቸው። እነዚህን እሴቶች መንግስት በሌላ መንገድ ከሚያስተምረው የበለጠ በሃይማኖት ተቋማት በኩል ፍሬ ሲያፈሩ የበለጠ ሃይል ይኖራቸዋልና መንግስት የሃይማኖትን ተቋማት በ ኣክብሮትና በ እንክብካቤ ሊይዛቸው ይገባል።
መንግስት በሃይማኖት ኣስተዳደር ኣካባቢ እጁን ሲያጠልቅ ኣባላት መንፈሳዊ ሽታ እየራቃቸው ይሄዳሉ። ይሰጋሉ። በተቋማቸው ያላቸው መተማመን እየቀነሰ ሲመጣ ደሞ ዞሮ ዞሮ የሚጎዱት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ የፍትህ ስርዓቱም ነው።
ዜጎች ምንም ሃይማኖት ባይኖራቸው የሚኖራቸው የህሊና ህግ ያን ያህል ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ምንም ሃይማኖት ከሌለ ምን ኣልባትም ገንዘብ ካለህ ሃምሳ የ ሃሰት ምስክር ለመሰብሰብ ላይከብድ ይችላል። በማህበራዊ ግንኙነት ጊዜ ተማምሎ የጋራ ስራ ለመስራት ኣስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት የሌለው ሁሉ ኣይታመንም ማለት ኣይደለም። ኣሉ ኣንዳንድ ዳኞች ለ ሙያቸው የሚሞቱ ኣሉ ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ለ ኣላማቸው የሚሞቱ፣ ይሁን እንጂ በሰፊው እንዳገር እንደ ህዝብ ስናስበው ሃይማኖት ጠቃሚ ሃገርን እንደ መልህቅ የሚያቆም ትልቅ የተከበረ ተቋም ነው።
ለነገሩ በሃገራችን መንግስት በ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የጀመረው በ ደርግ ጊዜ ነበር። ደርጉ የ ሶሻሊዝምን ስርዓት እንገነባለን ብሎ ባበደበት ሰኣት “ጎታች” ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት መካከል ኣንዱ ነበሩ። ዝግ እያለ ገብቶ ቄሱን ሁሉ የጾም እንዲበሉ በማድረግ የ ኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን እምነት ሊያስጥል ሞክሯል፤ ጎድቷታልም። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በፊት ለፊት ሲገድልና ሲያስር እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ኢህኣዴግ ሲመጣ የተሻለ ነገር ይመጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር። በተለይ መንገላታት ያደከመው የፕሮቴስታንቱ ኣማኝ ኣንጻራዊ ነጻነት ያገኛል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ራሳቸው የኢህኣዴግ ካድሬዎች በፈጠሩት ቀውስ በተለይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ብዙ የፕሮቴስታንት ና የ ኦርቶዶክስ ሰዎች ተጋጭተው ብዙ ብዙ ጉዳት ደርሷል።
ኣሁን ደሞ የዜጎችን ቀልብ በመልካም ስራ መሳብ ያቃተው መንግስት ዜጎች ልባቸውን የጣሉበትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት እያሸተተ ዜጎችን ሊቆጣጠር ይፈልጋል። በተለይ በቅርብ ጊዜ የሚታየው የከፋ ነገር ደሞ በ ኢትዮጵያ ሙሲሞች ዘንድ መንግስት የሚያሳየው ኣስጸያፊ ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ ችግር ብዙ መዘዞችን ለሃገራችን ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ኣንዱና ትልቁ ችግር ኣክራሪነትን ይወልዳል የሚለው ስጋት ነው።
የሃይማኖት ሰዎች የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄ ሲያነሱ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ መብት ከሚታገሉት የከረረና የመረረ ነው። ከሁሉም በላይ የሃይማኖት ደጃቸው ሲደፈር፣ ኣምላካቸው ሲያዝን ስለሚታያቸው ቁጣቸው ይበዛል። መስዋእትነት ለመክፈልም ቢሆን ለ ሃይማኖታቸው ለ ኣምላካቸው ቢሞቱ በሰማይ ብድራት ስላላቸው ኣይፈሩም።በመሆኑም በሃይማኖት በኩል የሚመጣ ቁጣ እንዲህ በቀላሉ ኣይበርድም። ከሁሉ የሚከፋው ግን በሃይማኖቱ ውስጥ ካሉ ኣባላት ውስጥ በጣም ኣጥባቂ ያልሆኑትን ወደ ሌላ ጽንፍ እየወረወራቸው እልህና ቁጣ ይሞሉና ኣክራሪ ኣሸባሪ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጥያቄያቸው እየከረረ ሲሄድ ኣመጹ ራሱ ከሚፈጥራቸው ኣንዳንድ መሪዎች መካከል የሚነሳ ኣስተምህሮም ሊፈጠር ይችላል። ከሁሉም በላይ ሃይማኖታቸው ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ይጀምሩና ኣክራሪነት እየተወለደ ሊመጣ ይችላል። ዛሬ በኣለማችን ያሉ ኣክራሪዎች የተወለዱት ከ መልካም ኣስተዳደር እጦት ከመብት ገፈፋ ጋር እየተያያዙ የመጡ ናቸውና፡፡
መንግስት ሊረዳው የሚገባው ነገር
የ ሃይማኖት ጥያቄ የሚፈታው በፖለቲካዊ መንገድ ኣለመሆኑን ነው። ልክ የፖለቲካ መብት እንዳነሱ ኣይነት በቴለቪዥን “ህጉንና ህገ
መንግስቱን ኣክብረው መኖር ኣለባቸው” የሚባል ፈሊጥ መልስ ኣይሆንም፡፡ ኣያስፈራቸውምም። የሃይማኖትን ችግር በሸምግልናና በትህትና
በሃይማኖት ሰዎች በኩል መፍታት ያስፈልጋል። ኢህኣዴግ የ ሙስሊሙን ጤያቄ ሌሎች የ ህዝብ ኣመጾችን በሚያፍንበት የዘወትር መሳሪያው
ሊያበርደው ኣለመቻሉን መረዳት ኣለብት።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
No comments:
Post a Comment