እጅግ የማከብራችሁ የሃይማኖት መሪዎች፣ ታላላቆቼ የቀደመው ትውልድ አባላት እንዲሁም የእለቱ የክብር እንግዳችንና በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ላይ በተደጋጋሚ ያኮራን ጀግናው አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ፣ እንዲሁም ይህንን በዓል ለማክበር የታደማችሁ እህቶቼና ወንድሞቼ፣ ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ ቆሜ ስለቀደሙት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ገድል በመናገሬ ትልቅ ክብርና ደስታ ተሰምቶኛል። ይህን ፕሮግራም ላዘጋጁት የኮሚቴ አባላት ከፍ ያለ ምስጋናየን እያቀረብኩ በዚህ ፕሮግራም ላይ እንድናገር ስለጋበዙኝ የዚህን ፕሮግራም አቀናባሪዎች በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ።
ያ የቀደመው የአጼ ምኒልክ ትውልድ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ በአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ በደሙ ደማቅ ታሪክ የጻፈ ትውልድ ነው። ዛሬ የነዚያን ጀግኖች እናቶችና አባቶች ገድል ስናስብ ጥልቀት ባለው መረዳት ላይ ቆመን መሆን አለበት::
ኢትዮጵያውያን የአድዋን ድል በዓል ስናከብር ሁል ጊዜም በትኩረት ልናስባቸው የሚገቡ 4 ጉዳዮች አሉ። አንደኛው የዓድዋ ድል አንጸባራቂ፣ ድርብ ድል መሆኑን መገንዘብ፣ ሁለተኛ የዓድዋው ጦርነት ዓላማ ምን እንደሆነ በጥብቅ መረዳት፣ ሶስተኛ የዓድዋ ድል ያምጣቸውን ዓለማቀፍ ተጽእኖዎች ማወቅና አራተኛ ትውልድ ኣልፎ ትውልድ ሲተካ በትውልዶች መሃል ይህን የከበረ ድል የምንጠብቅ ትውልድ መሆናችንን በየዘመኑ ራሳችንን መፈተሽ ናቸው።
አድዋ ድርብ ድል የየዘ አንጸባራቂ ድል ነው ስንል እንደሚታወቀው በየካቲት ወር የምናከብረው በዓል ኢትዮጵያ ቅኝ ሊገዛት ካሰባት የጣሊያን ሰራዊት ጋር ሜጀር ውጊያ አድርጋ የተገኘውን የሚሊተሪ ድል እያሰብን ነው። ከዚህ ወታደራዊ ድል በተጨማሪ ኢትዮጵያ የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ ማድረጓ አንዱ ታላቅ ድልነው። የውጫሌውስምምነት አንቀጽ ኣስራ ሰባት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስራ ላይ ጣሊያን ጣልቃ እንድትገባ ከዚያም ኣልፎ ኢትዮጵያ በጣሊያን ይሁንታ የውጭ ግንኙነት ስራዋን እንድትሰራ የሚጠይቅ ስምምነት ሲሆን ይህ ኣንቀጽ ሲተነተን የኢትዮጵያን ልእልና የሚነካ በመሆኑና አንቀጹ የቅኝ ግዛት ኣንቀጽ በመሆኑ ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ይህንን አንቀጽ ውድቅ ኣደረጉ። ኢትዮጵያችን ይህን ኣንቀጽ ውድቅ ማድረጓ በራሱ በቅኝ ግዛት ላይ የተደረገ ድል ነበር። እ. አ. አ. በ 1884/85 ዓ.ም ቅኝ ገዢ ሃገራት በርሊን ላይ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ቅኝ ገዢ ሃገራት ሁሉ የተስማሙበት ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ስምምነቱ የበርሊን ስምምነት በመባል ይታወቃል። ይህ ስምምነት የተፈረመው ቅኝ ገዢዎች እርስ በርስ ሳይጋጩ በሰላም አፍሪካን እንዲቀራመቱ ነው። በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ኣንስተው እንዳይጋጩ የሚያስበው ይህ ኮንቬንሽን ኣፍሪካን በገሃድ የመቀራመት ኮንቬሽን ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ከቀይ ባህር ማዶ የምተገኝ ኣፍሪካዊት ኣገር ይህንን ስምምነት ውድቅ ኣደረገች አይሞከርም አለች። ኢትዮጵያ በምድረበዳ እንደበቀለች ኣበባ ብቻዋን በአፍሪካ ምድር በዚያ ቀውጢ ወቅት የቅኝ ግዛትን ስምምነት ውድቅ ማድረጓን በውጫሌው ስምምነት ያሳየች የጀግኖች ሃገር ናት። ይህ ድል በራሱ ግዙፍ ድል ነው። ኢትዮጵያ የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ ስታደርግ ጣሊያን ይህንን ተቀብላ አርፋ ብትቀመጥ የውጫሌው ስምምነት ውድቅ መደረጉን ለብቻው ስናከብረው የምንኖረው ድል ይሆን ነበር።
የውጫሌውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ኣልቀበልም ማለት የበርሊኑን ስምምነት ኣልቀበልም፣ ቅኝ ግዛትን አልቀበልም፣ አፍሪካን በሃይል ቅኝ መግዛት ኣይቻልም ማለት ነውና ይህ የአባቶቻችን ድምጽ ዘወትር ሲከበር ይኖር ነበር። ነገር ግን የውጫሌውን ስምምነት ኢትዮጵያ ውድቅ ስታደርግ ጣሊያን የወሰደችው ርምጃ ወታደራዊ ሃይል ነበር። ኢትዮጵያ በሰላም ቅኝ ኣልገዛም ካለች በወታደራዊ ሃይል ትገዛ የሚል ትእዛዝ ከጣሊያኑ ንጉስ ንጉስ ኡምቤርቶ በመውጣቱ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወታደራዊ ሃይል ድባቅ መታ ቅኝ ለመግዛት ተንቀሳቀሰች። ከዚህ በሁዋላ ታሪክ ዘወትር የሚዘክራቸው ጀግናው አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከዳር ኣስተባብረው በአድዋ ተራሮች ላይ ወታደራዊ ፍልሚያ ለማድረግ በእግር በፈረስ ወንድማቸው ትግራይ ህዝብ ዘንድ አይዞን ደደርሰንልሃል አሉ። የትግራይ ህዝብም ጠብ እርግፍ እያለ ወገኑን እያስተናገደ ለጋራው ፍልሚያ ጋሻና ጦሩን አነሳና አብሮ ተሰለፈ። የትግራይ ሴቶች የኣማራ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የምስራቅ እህቶቻቸውን እየተንከባከቡ የእቴጌን ባታሊዩን ተቀላቀሉ። ትግራይ ብዙ ተጉዘው የመጡ ወንድሞቹን የጓጎለ እግር እያሸ የፍቅርን የአንድነትን ጥግ ኣስየ። በአጼ ምኒልክ የሚመራው ጠቅላላ ጦር ጉዞው ቀላል አልነበረም። ወርና ከወር በላይ የፈጀ የእግር ጉዞ ነው። በጉዞው ወቅት የሞቱ ሰውነታቸው የተጎዳ ወገኖች ብዙ መኖራቸው አይቀርም።
በዚህ ጦርነት ላይ ያልተሳተፈ የለም። በየግዛቱ ሸፍተው የነበሩ፣ በመንግስት ላይ ኣምጸው የነበሩ ሳይቀሩ የአጼ ምኒልክን ጉልበት እየሳሙ ይቅርታ እየጠየቁ በዚህ ጦርነት ላይ በአንድነት ተሳትፈዋል። ታዲያ በአድዋ ተራሮች የትግል ኣውድማ ላይ ኢትዮጵያውያን አንድ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ድል በማስመዝገባቸው የቅኝ ግዛቱን የሃይል ሙኩራ በድል ዘጉት። ያ ትውልድ በአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ በደሙ ደማቅ ታሪክ ጻፈ። አድዋን ስናስብ ድላችን ባለ ድርብ ድል ነው ስንል ኢትዮጵያ የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ በማድረጓ የተገኘው ድል ሲደመር በአድዋ ተራሮች ላይ የተገኘውን ወታደራዊ ድል እያሰብን መሆን አለበት።
የዚህ የአድዋ ጦርነት ዓላማም ይሁን የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ ያደረግንበት ዓላማ ነጻነትና ብሄራዊ ልእልና ነው። ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት ውል እምቢኝ ስትልና ውድቅ ስታደርግ፣ በሃይል በወታደር ቅኝ ልግዛሽ ሲላት ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንድተነካበት ንብ ብድግ ብለው የሚነሱት ለነጻነትና ለብሄራዊ ልእልናቸው ላቅ ያለ ክብር ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛቱ ዘመን ቅኝ አለመገዛቷ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ደካማ ፈላልጋ ቅኝ ለመግዛት አለመሞከሯ ለቅኝ ግዛት ያላትን አመለካከት ለነጻነት ለአፍሪካ ነጻነት ያላትን ክብርና ቁርጠኝነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሚያኮራን ታሪክ በቅኝ ግዛት አለመገዛታችን ብቻ ሳይሆን ለመግዛት አለመሞከራችንም ነው።
የአድዋ ድል መንፈስ የነጻነት የእኩልነት መንፍስ ነው። የአድዋ ድል ዘርና ቀለምን መሰረት ያደረገ ጦርነት ሳይሆን በሃገር ልእልና ላይ የተቃጣ ጥቃትን የመከተ ድል ነው። እንደሚታወቀው ቅኝ ግዛት የዘርና የቀለም ንቅናቄ አልነበረውም። ቅኝ ግዛት ዘርና ቀለም ሳይለይ በዓለም ላይ የተከሰተ ነገር ነው።
ህንዶች በእንግሊዞች ቅኝ ተገዝተዋል፣ ፓርቹጋሎች ብራዚልን ቅኝ ገዝተዋል፣ ጃፓኖች ኮርያውያንን ቅኝ ገዝተዋል፣ ሜክሲኮዎች በስፔን ተገዝተዋል፣ ሶርያውያን በፈረንሳዮች ተገዝተዋል። ግብጾች በእንግሊዞች ተገዝተዋል፣ ሊባኖሶች በፈረንሳዮች ተገዝተዋል። እንዳንዶቹ ሃገራት ደግሞ ሁለት ቅኝ ገዢዎች እየተፈራረቁባቸው ተገዝተዋል። ሩዋንዳ አንዴ በጀርመን አንዴ በቤልጂየም ተገዝታለች። በአጠቃላይ የቅኝ ግዛት የሚባለው ነገር የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ ነው። ይህ ፖሊሲ ጉልበት ያለው መንግስት ጉልበት የሌለውን በማንበርከክ ቅኝ ገዚዎች በቅኝ ተገዢዎች ጫንቃ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን ማምጣት ነው፣ ግዛትን ማስፋፋት ነው። ይህ ፖሊሲ ታዲያ ውሎ ኣድሮ ለራሳቸው ለቅኝ ገዢ ሃገራትም ሳያዋጣ ቀርቶ ብዙ ዋጋ ያሰከፈላቸው ሆኖ አልፏል። ኢትዮጵያ ዓለም በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ስትቃወምና ድል ስታደርግ በዓለም ላይ ድል የመታችው ራሱን ቅኝ ግዛትን ነው።
የታሪክ ምሁር የሆነውና The Battle of Adwa. African victory in the age of
empire. የተባለውን መጽሃፍ የጻፈው ፕሮፌሰር Raymond
Jonas የአድዋን ድል ውጤት ሲገልጸው "This is the story of
a world turned upside down" ይለዋል። የኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል በርግጥም የዓለምን ፖለቲካ የገለበጠ ነበር። በዓለም መድረክ በዲፕሎማሲው የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ በማድረግ የቅኝግዛቱን የሃይል ንቅናቄ በተገቢው ወታደራዊ ሃይል በመምታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ድል ለዓለም ህዝብ ብርቅየ ነው። በተለይም ኣፍርሪካውያን እንደ አህጉራቸው ልጅ በኢትዮጵያውያን ድል መኩራት ብቻ ሳይሆን የአድዋን ድል በየዓመቱ ክብረ በዓላቸው ሊያደርጉት ይገባል።
የአድዋ ድል ያመጣው አንድ አስደናቂ ውጤት የሃይማኖት ነጻነትን ማምጣቱ ነው። በተለይ ጥቁሮች ከአድዋ ድል በሁዋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እያሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ተከሉ:: በደቡብ አፍሪካ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተቋቁመው ነበር። በአሜሪካ የአቢሲኒያ ቤተክርስቲያን የተቋቋመው ከአድዋው ድል በፊት ቢሆንም ጥቁሮች በአቢሲኒያ የረጅም ጊዜ የነጻነት ታሪክ ኢትዮጵያን መመኪያ በማድረጋቸው ነው። በዚያን ወቅት በተለይ ጥቁሮች ቄስ መሆን አይችሉም፣ መጋቢ መሆን ኣይችሉም፣ የራሳቸው ቤተክርስቲያን ሊኖራቸው ኣይችልም እየተባሉ የሃይማኖት ነጻነታቸው ተገፎ በአምላካቸውና በጥቁሮቹ መሃል ግድግዳ ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ጊዜ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች” የሚለውን ቃል አጼ ምኒልክ ከፍ ኣድርገው በመያዝ የታገሉ ሲሆን እነሆ ዛሬ ፍሬያቸው ዓለምን ሞልቷል። አቢስኒያ በዚህ ረገድ ያገኘችው ድል ለዓለም ህዝብ መንፈሳዊ ድልን አጎናጽፏል።
ኢትዮጵያ የውጫሌውን ስምምነት ውድቅ ኣድርጋ በወታደራዊ የመከላከል ንቅናቄዋ አንጸባራቂ ድል ካስመዘገበች በሁዋላ ብዙ ለውጦችን ኣይታለች። ጎረቤት ሃገሮችን ቅኝ የገዙ ሃገራት ለአጼ ምኒልክ የድንበር ስምምነት ጥያቄ እያቀረቡላቸው እስከ 1908 ድረስ የሰላምና የድንበር ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አድርጓል። ሌላው ጉልህ ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የሚያስቡ ሁሉ እንዲማሩ ኣድርጓል። የቀድሞው የደቡብ ኣፍሪካ ፕሬዚደንት ታቦን ቤኪ ሲናገሩ አንድ የሚያውቁት የጃፓን መንግስት ኣማካሪ የነበረ ሰው የነገራቸውን ሲገልጹ እንዲህ አሉ።
ጃፓን ከሩቅ ምስራቅ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ኣስባ ነበር። የጃፓኑ ንጉስ ካርታ እያዩ ኢትዮጵያን አየጠቆሙ ይህቺን ኣገር ቅኝ ለመግዛት እፈልጋለሁ ይሉ ነበር። ኢትዮጵያን በጣም ተመኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ሙከራ ባደርግ የአድዋው ዱላ ኣይቀርልኝም ብላ ይሆናል ኣሳቧን በጠዋቱ ሰርዛለች። ጃፓን ዘየደች::
ሌላው የአድዋ ድል ትልቁ ውጤት በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያመጣው የመተዋወቅ፣ የአንድነት መንፈስ ነው። የሃገርን ጽንሰ ሃሳብ በጣም ያዳበረ ታሪካዊ ክስተት ነበር። ብዝሃነታችንን ከአንድነታችን ጋር የሚያያይዝ ታሪካዊ መድረክ ነበር። ለማእከላዊ መንግስት መጠናከር ጉልህ ሚና ተጫውቷል። አንድ ሆነን እንደ ሺህ ሺህ ሆነን እንደ ኣንድ የምንኖርበትን ረቂቅ ኣሳብ በተግባር ያሳየ መድረክ ነው። የአድዋ ድል እኛ ከምናውቀውና ከምናስበው ከገመትነው በላይ ለብዙ የተጨቆኑ ነጻነት ፈላጊ ህዝቦች መጽናኛ ሆኗል።በአድዋው ድል ማግስት በብዙ ዓለም የአጼ ምኒልክ ስም ናኝቶ ነበር። በፖርቹጋሎች ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የብራዚል ጥቁር ጭቁኖች ምኒልክን አወድሰዋል። ምኒልክ በዓለም የነጻነት ታጋዮች ዘንድ ብዙ ግርማና ሞገስ ኣግኝተዋል።
ያ የእምየ ምኒልክ ትውልድ ጀግኖች፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የሰሜን የደቡብ የምስራቅ የምእራብ ልጆች በርግጥ በአድዋ ተራሮች ላይ እየተወነጨፉ፣ እየፎከሩ፣ ለሃገራቸው ነጻነት ከቅኝ ገዢው የጣሊያን ወታደር ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተያይዘው በዚያ የውጊያ ኣውድማ ላይ ድል የነሱ ተራሮችን ያንቀጠቀጡ ትውልድ ናቸው። ክፍለ ኣህጉራዊ intercontinental ውጊያ ገጥሟቸው በድል የተወጡ አባቶቻችን በርግጥ እነሱ ተራሮችን ያንቀጠቀጡ ናቸውና ዘላለም ክብር ይገባቸዋል። ታዲያ የአድዋ ገድል ሲነሳና እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን ድል ስናከብር ጀግናይቱን እቴጌ ጣይቱንና ጀግናውን አልፈርድ ኢልግን ሁል ጊዜም፣ ምን ጊዜም አንዘነጋም። እቴጌ ጣይቱ የአጼ ምኒልክ ኣጋዥ ብቻ ሳይሆኑ ግሩም መሪ ነበሩና ለዛሬዎቹ እህቶቻችን የሰነቁት የሞራል ስንቅ፣ ጥለው የሄዱት ሌጋሲ እንዲህ በቃል ኣይገለጽም። ሰለ አድዋ ድል ስናስብ ብዙ ጊዜ አባቶቻችን የሰሩትን ገድል ነው የምናጎላው። ነገር ግን እናቶቻችንም በዚህ ፍልሚያ ውስጥ አኩሪ ጀግንነት ፈጽመዋል። ከሴቶቹ መሃል ተወርዋሪ ኮከቧ እቴጌ ጣይቱ ሲሆኑ በስራቸው የሚታዘዝ እስክ ሶስት ሺህ የሚደርስ ጦርን ግራና ቀኝ ግንባር ላይ አንድ ብርጌድ ጦር የመሩ ጀግና ናቸው። ምን አልባትም እቴጌ ጣይቱ ይመሩት ከነበረው አንድ ብርጌድ ጦር ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የቴጌ ጣይቱ ባታሊዩን የሴቶች ብርጌድ ይሆናል። እቴጌ የውጫሌው ስምምነት ውድቅ እንዲሆን የተጫወቱት ሚና በታሪክ ጉልህ ቦታ ያለው ሌላው የማይረሳ ተግባራቸው ነው። እቴጌ ጣይቱ የብርጌድ ኣዛኝ፣ ኣስተባባሪ፣ አልሞ ተኳሽ፣ መድፋ አስተኳሽና ተወርዋሪ ተዋጊ ብቻ ሳይሆኑ የጸሎት ሰውም ነበሩ። በጣም መንፈሳዊ ሰውም ነበሩ። በአድዋ ተራሮች ላይ ተንበርክከው ለሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ ያደሩበት ጊዜ ነበር። አምላካቸው ለባለቤታቸው ብርታትን እንዲሰጥ፣ ለኢትዮጵያ ጦር ድልን እንዲሰጥ ተማጽነዋል። እቴጌይቱ ታሪክ ዘወትር የሚዘክራቸው ባለ ሙሉ ግርማ መሪ ናቸው። ወጣት ኢትዮጵያውያን እህቶቼ የጣይቱ ልጆች ናችሁና ልትኮሩ ይገባል። ይህንን የጣይቱን መንፈስም ልትጠብቁ ይገባል።
በአድዋው ጦርነት ላይ ከተሳተፉት ሴቶች ውስጥ ሌሎች ሴቶች በተለይም መበለቶችና ከባሎቻቸው ጋር እሞታለሁ ያሉ ሴቶች ሁሉ በጦር አውድማው ላይ ቃታ እየሳቡ ይዋደቁ ነበር። እጅግ ብዙ ሴቶች ደግሞ ለሰራዊቱ የሚሆነውን ምግብ በማዘጋጀት የቆሰለን በመንከባከብ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሰራዊቱ የሞራል ድጋፍ በማድረግ በአድዋ ጦርነት ውስጥ ዘመን የማይሽረውን የድል ኣሻራ ትተው ኣልፈዋል። ስለሆነም የአድዋ ድል የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ድል ነው። ቀሳውስት ታቦት ይዘው ካህናት በዜማ በጦርነቱ መሃል እግዚአብሄር ሃያል በሰልፍም መሃል ሃያል እያሉ አምላካቸው በዚህ የውጊያ እውድማ ላይ ድል እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል። በርግጥም የእስራኤል አምላክ ድንበራቸውን አልፎ በመጣው ጦር ላይ ድልን ሰጥቷቸው በአድዋ ተራሮች ላይ አጊጠዋል:: ካህናት በጽናጽል በከበሮና በእምቢልታ የድል ዝማሬን አዚመዋል።
የስዊዘርላንዱ ተወላጅ ኣልፈርድ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበት ሃያ ስምን ኣመት ገደማ የአጼ ምኒልክ ታማኝ ኣማካሪ አጼ ምኒልክ እጅግ የሚወዱትና የሚያምኑት ጓዳቸው ነበር። ኣልፈርድ ኢልግ በምህንድስና ሙያው ኢትዮጵያን ያራመደ የመጀመሪያውን የቧንቧ ውሃ ፣መብራት፣ የባቡር መስመር የዘረጋ ብቻ ሳይሆን በውጭ ጉዳይ ስራዎች ኢትዮጵያውያን ምን ጊዜም የማንረሳውን ውለታ ጥሎብን የሄደ ጀግናችን ነው። ኣልፈርድ የውጫሌውን ኣደናጋሪ ትርጉም የሚኖረውን ዓለማቀፋዊ ፖለቲካዊ አንድምታ ቁልጭ ኣድርጎ ለአጼ ምኒልክ አስረድቷል:: አልፈርድ አጼ ምኒልክ ውሉን ውድቅ እንዲያደርጉ የተጫወተው ሚና በነጻነት ፈላጊዎች ዘንድ ሊታወስ የሚገባው መታሰቢያ ሊቆምለት የሚገባ ጀግና ነው። ኣልፈርድ ከአድዋ ድል በሁዋላ ወደ ሃገሩ ተመልሶ ለአንድ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ “እኛ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ኣድርገናል!” ሲል በኩራት ተናግሯል። አልፈርድን እኛም እንኮራበታለን። ኣልፈርድ ከኢትዮጵያውያን ጋር ከአጼ ምኒልክ ጋር የገባውን ኪዳን የጠበቀ ጀግና ነውና ሁሌም እናስበዋለን፣ እንሸልመዋለን።
ራስ መኮንን፣ ራስ ቢትወደድ፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ አሉላ፣ ደጃዝማ ወልዴ፣ ፊታውራሪ ገብሬ፣ ፊታውራሪ ተክሌ፣ የዋግ ሹሙ ጓንጉል፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ሊቀመኳስ አድነው፣ ቀኝ ኣዝማች ታፈሰ፣ ራስ ኣባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስና ሌሎች የጦር መሪዎች መታሰቢያ የሚሹ ትውልድ ሁል ጊዜም የሚኮራባቸው ጀግኖቻችን ናቸው። አድዋን ስናስብ የነዚህን ጀግኖች የጦር መሪዎች ገድል እንዘክራለን። ለወታደራዊ ድል የሚሊተሪ ኢንተለጀንስ ዋና ጉዳይ ነው። በአድዋው ጦርነት ድል በወታደራዊ ኢንተለጀንስ ስራው ሃገራችን የምትኮራበት ጀግናው ባሻ አዋሎም መታሰቢያ ያስፈልገዋል። ሌት ከቀን እየተመላለሰ ሃገሩ የምትኮራበትን ታላቅ የስለላ ስራ በብቃትና በሃገር ፍቅር የተወጣ ጀግና ነውና ባሻ አዋሎም የሁላችን ጀግና ነው።
እንግዲህ እነዚያ በአድዋ ተራሮች ላይ የሰፈሩት አንዳንዶቹ አማሮች፣ አንዳንዶቹ ትግሬዎች፣ አንዳንዶቹ ኦሮሞዎች፣ አንዳንዶቹ ከደቡብ፣ አንዳንዶቹ ከምስራቅ፣ አንዳንዶቹ ከምእራብ የመጡ ነገር ግን የአንድ እናት ልጆች የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። እነዚህ የአንድ እናት ልጆች በአድዋ ተራሮች ላይ በቋንቋ አይግባቡም ነበር። ነገር ግን በመንፈስ ይግባቡ ነበር። ቋንቋ ያላገደው መግባባት በአድዋው የጦርነት አውድ ላይ ትርዒት ታይቷል። እነዚህ ከተለያየ ብሄር የመጡ የጦር መሪዎች በአድዋ ተራሮች ላይ በደማቸው የህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ጽፈው ያለፉ ናቸው። ኢትዮጵያ በዚህ መሰረት ላይ የቆመች የሁላችን ለሁላችን ኣገር ነችና የኛ ትውልድ ይህንን መሰረት እያጽና ብዙ ሆነን እንደ ኣንድ ኣንድ ሆነን እንደ ብዙ ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ሰላም ልንሰራ ይገባል። እነዚህ ጀግኖች በተለይ በችግር ጊዜ አንድነት፣ መደጋገፍን እንጂ መለያየትን አላስተማሩንም። እነዚህ ጀግኖች ዛሬ ቀና ብለው ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? ብለን እኛ ኢትዮጵያውያን መመርመር አለብን። እርግጥ ነው በቀደሙት አባቶች እንኮራለን። ልንኮራም ይገባል። ነገር ግን ይህንን ድል ለመጠበቅ እነዚያ አድዋ ላይ የወደቁ አባቶችና እናቶች ቀና ብለው ቢያዩ አሁን እኛ ባለንበት ሁኔታ ይኮራሉ ወይ? ብለን ራሳችንን መመርመር አለብን። የአድዋን ድል ስናከብር የአድዋን የነጻነት የእኩልነት የአንድነት መንፈስ ኣጥብቀን ይዘን መሆን አለበት። አለበለዚያ ከንቱ ውዳሴ ይሆንብናል። አባቶች የሞቱት ለዚህ ነውና። የኛ ትውልድ ከአድዋ የሚማረው አንደኛ በተለይ በክፉ ጊዜ አንድነትን፣ ሁለተኛ ለነጻነት መስዋእትነትን አለመፍራትን፣ ሶስተኛ ለነጻነት የሌሎችን መስዋእትነት አለመጠበቅን፣ አራተኛ መተሳሰብን ፍቅርን አንዱ ስለሌላው መኖርን ነው። ዛሬ ዓለም ተቀይሯል። ጣሊያን ትናንተና ጥቁር ናይጄሪያዊ ሴናተር አድርጋ መርጣለች። ዛሬ ጣሊያን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአደገኛ ጉዞ ሲሰደዱ ባህር ውስጥ እንዳይሰጥሙ ሌት ከቀን ትጥራልለች። የባህር ሃይሏ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከሞት እየታደገልን ነው። በዚህ ዘመን የአድዋን ድል የምንጠብቀው በቤታችን ውስጥ አንድነትን በማጠናከር፣ በብሄሮች መካከል ፍቅርን በማብዛት፣ አንዳችን ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም በመኖር ነው። አጼ ምኒልክ መላው ኢትዮጵያውያንን አነቃንቀው ወደ አድዋ ሲሄዱ ከጦሩ መሃል የወላይታውን ሹም ካዎ ጦናን፣ የጅማውን ሹም አባ ጅፋርን፣ የቤንሻንጉልና አካባቢውን ሹም ደጃዝማች ጆቴን፣ ከወለጋ የመጡትን ደጃዝማች ገብረእግዚአብሄርን ሁላችንም ጥርግ ብለን ስንሄድ መሃል ሃገር ባዶ ይቀራል በሚል ይህ ጦር መሃል ኣገር እንዲጠብቅ መልሰውታል። ይህ ማለት በንጉሱ የሚመራው ጦር አድዋ ላይ ቢሰዋም እነዚህ ወገኖች ሃገር ተረክበው ኢትዮጵያን እንዲመሩ ነው። ምኒልክ ወደ ጦር ሜዳ ሲያመሩ አንኮበርን ደጀን አድርገው ንጉስ ጦናን እሳት ላይ ኣልማገዱም። ምኒልክ ራሳቸውን ነው በአድዋ ተራራ ላይ ለመስዋእትነት ያቀረቡት። የቀደሙት ኣባቶች ያስተማሩን ይህንን ነው። ራስ መንገሻ ብቻቸውን እንዳይጠቁ፣ የትግራይ ህዝብ ጉዳት እንዳይደርስበት አጼ ምኒልክ ራስ መንገሻን ደርሰናል፣ እየመጣን ነው፣ አይዞህ ብለው ነው መልእክት የላኩት። ራስ መንገሻም የወገንን ጦር ሲጠባበቁ ቆይተው ወገን ሲደርስላቸው በደስታ ተቀብለው አብረው ተዋድቀዋል። ይህንን ነው ከቀደሙት አባቶቻችን የተማርነው። ኣንዳችን ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም መኖርን ነው ያስተማሩን ። አማራው ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም ይኖራል፣ ትግራዩ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም ይኖራል፣ ኦሮሞው እንደዚሁ እንዲህ ስናደርግ አንድነታችን ይጠነክራል። የአድዋን መንፈስም ጠበቅን ማለት ይሄ ነው። ዛሬ ጀግንነት የሚገለጸው በጦር በጎራዴ ብቻ ሳይሆን በሳይንስ በቴክኖሎጂ ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ተፎካካሪ በመሆን ነው። የአድዋ ድል ኣድራጊዎች ባለ ታሪክ ህዝቦች በምግብ እጥረት ስማችን ከተነሳ እልህ ሊይዘን ይገባል። የእኛ ትውልድ የአድዋን ድል የሚደግመው በየመስኩ ነው። እንደ በላይነህ ዲንሳሞ ሯጮች በሩጫው መድረክ፣ ተማሪው በትምህርቱ፣ አርቲስቱ በሙያው፣ ፖለቲከኛው ወደ ዴሞክራሲ በመሻገር ቢያንስ በሌሎች ኣፍሪካ ሃገራት ሳይበለጥ አንደኛ መውጣት አማራጭ የፖለቲካ አቅጣቻዎችን፣ ፖሊሲዎችን መፍጠር፣ ሙያተኛው በሙያው በሚያደርገው ሩጫ አሸናፊ በመሆን ነው ። ውድድራችን ብሄር ከብሄር ይሆን ዘንድ ኣድዋ ኣላስተማረችንም። ኦሮሞው ከትግሬው፣ ትግሬው ከአማራው፣ ደቡቡ ከምስራቁ፣ ምእራቡ ከሰሜኑ ኣይደለም የሚታገለው። በጎ ሩጫችን ከሌላው ዓለም ጋር እንዲሆን ነው አድዋ ያስተማረችን። እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ይህን የአድዋን ድል መንፈስ የምንጠብቅ ጀግኖች ነን። እግዚኣብሄር የኢትዮጵያ አምላክ ዛሬም ከኛ ጋር ነው። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ዘርግታለችና የተሻለ ዘመን ከፊታችን አለ። እንሻገር።
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
https://www.facebook.com/enqutatashboston/?hc_ref=ARStt_zaG1T6oczmJBtg2pLD4bm2_Qm4xYKRZ1coWk6mqX3vqYdCd7fl5HSUd4vH474&fref=gs&dti=1291048757672648&hc_location=group
https://www.facebook.com/enqutatashboston/videos/189983491606575/