ገለታዉ ዘለቀ
ከባለፋው የቀጠለ
ክፍል ስድስትበስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል አንድነት (CCU) የእድገት አቅጣጫዎች
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ባህል አዳጊ ነው፡፡ ባህል በተፈጥሮው ዳይናሚክ በመሆኑ በኣንድ ቡድን ህይወት ውስጥ ትውልዶች በራሳቸው ዘመን የየራሳቸውን ፈጠራ እየጨመሩበት ወደላይ ያድጋል:: በሌላ በኩል ደሞ ባህል ወደ ጎን ካለው ሌላ ቡድን ጋር ሲነካካ(interact ሲያደርግ) እሴት እየተጋባ ወደ ጎንም ያድጋል።ወደ ጎን ሲያድግ ብዙ ያጋራ እሴቶችን ስለሚገነባ የነዚያ እሴቶች ያዢ(holders) ሁሉም ቡድኖች ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ያደረገውም እነዚህን ሁለት የባህል የእድገት ኣቅጣጫዎች ነው።
ሌላው የዚህ ንድፈ ሃሳብ መነሻ ደግሞ ሊመልሰው የሚገባ አንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህም በስምምነት ላይ የሚደረግ
የባህል ውህደት ኣንዱ ግቡ አንድነት ሲሆን የዚህ ንድፈ ሃሳብ የመጨረሻ ግብ (ultimate goal) ሄዶ… ሄዶ…. አንድ ነጠለ ህዝብ (homogeneous society) ለመፍጠር
ይመስላል የሚል ጥያቄ ይሆናል፡፡ በመሰረቱ ግን የዚህ ንድፍ ሃሳብ አላማ ይሄ አይደለም፡፡ ዓላማው ወደ ላይም ወደ
ጎንም ባህል ሊያድግ ስለሚችል ቋንቋዎች ዘላለም የሚኖሩበትን፣ ቡድኖች ዘላለም የሚኖሩበትን በአንጻሩ ጥበባቸውን እየተካፈሉ ወደ
ጎንም እያደጉ መሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው፡፡ እንዴት ወደ ላይ ወደ ጎንም ይታደጋል? ካልን እንዴት አንድ ሰው ሁለት ቋንቋ ሊናገር አይችልም በሚል አጸፋ እንመልሳለን፡፡ ይቻላል፡፡
ሁልጊዜም ወደ ሁለት አቅጣጫ ማደግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቡድኖች ወደ ላይ /vertical/ እድገት ባንድ በኩል
እያሳዩ ወደ ጎን /horizontal/ እድገት በማሳየት የጋራ እሴት
እየገነቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ቡድኖች በስምምነታቸው ጊዜ ህገ-መንግስታቸውን፣ የሃይማኖት ተቋሞቻቸውን፣
ባህላዊ ቡድናቸውን ይዘው ኪዳን ሲገቡ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለኢትዮጵያዊነት ይሰዋሉ፡፡ ይህን መስዋዕት ካደረጉ በኃላ ኢትዮጵያ
መልሳ ቋንቋና ባህል እንዲንከባከቡ ለቡድኖች ትሰጣለች፡፡ ንብረትነቱ ግን የቡድኖቹ ብቻ ሰይሆን የኢትዮጵያዊነት ይሆናል ብለናል፡፡
በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተወለደበት ማህበረሰብ ውስጥ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪና የባህሉ ተካፋይ እስከሆነ
ድረስ ከባህላዊ ቡድነኝነት አንጻር የዚያ ቡድን አባል ይሆናል ማለት ነው፡፡ እናትና አባት ኦሮሞ ሆነው ልጅ አማራ የመሆን መብት አለው፡፡ ቋንቋና ባህል
ውጪያዊ ልምምድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህሎችና ቋንቋዎች የኢትዮጵያዊነት በመሆናቸው ዜጎች በዜግነታቸው ያገኙዋቸው
መብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በኦሮሞ ህዝብ ቸርነትና ፍቅር ልቧ የተነካው የእኔ እናት ኦሮሞ የመሆን መብቷም ይጠበቅላታል፡፡ በዚህ
ስምምነት ጊዜ ቡድኖች ክፍት ሆነው ግን ቋንቋና ባህላቸውን ለማሳደግ ጠንቃቃዎች ይሆናሉ፡፡
ከፍል
ሰባት
በዚህ
ንድፈ ሃሳብ መሰረት የብሄራዊ ቋንቋና የስራ ቋንቋ ጉዳይ እንዴት ይታያል?
በመጀመሪያ ደረጃ ዜጎች ይህንን ጥያቄ ሊያዩት የሚገባው ከገቡት ኪዳን አንጻር ነው፡፡ በዚያ
ከፍታ ላይ ሆነው ሲያዩ ቋንቋዎች ሁሉ ብሄራዊ ናቸው።የኢትዮጵያ ሃብት የሆኑ ቋንቋዎች ለምሳሌ ኣፋርኛ፣ ኣገውኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣
ወዘተ. ብሄራዊ ቋንቋ ተብለው ይጠራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ቋንቋዎች ብሄራዊ ናቸው ሲባል ከፍ ሲል በሰጠነው የስምምነት
መነሻ ኣሳብ ላይ ከተስማሙ የነዚህ ቋንቋዎች ሁሉ ባለቤት ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ ቡድኖችም ቋንቋዎቻቸውን ይዘው ሆ! ብለው መስዋእት
ስላደረጉ በመብት ደረጃ ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ብሄራዊ ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ኣንድ ወይም ከኣንድ በላይ
ቋንቋ መርጠው ዋና መግባቢያ ይኖራቸዋል። ዋና የስራ ቋንቋ ሲመርጡ ምናልባትም የሚያዩት አብዘኛው ህዝብ የሚናገረውን ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን ከዚያ በመለስ በቁጥሩ ከፍ ያለ ህዝብ የሚናገራቸው ሌሎች ቋንቋዎችም ካሉ እነሱንም አካቶ ዋና ቋንቋን ሁለት ወይም ከዚያ
በላይ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሁኔታ አማርኛና ኦሮምኛን ዋና ቋንቋ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ እንግሊዘኛንም በስራ
ቋንቋ ውስጥ በማካተት በአለም ተፎካካሪ ለመሆን ሶሊዳሪቲ ለማሳየት ይጠቅማል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በቋንቋ ጉዳይ እንዳይጋጩ ይህ በስምምነት
ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት እንደ መልህቅ ይይዛቸዋል፡፡ ይህ ስምምነት ሲወርድ በዋና ቋንቋ ምርጫ ጊዜ የኦሮምኛ ቋንቋ ዋና ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጋር ሊሰራ ይገበዋል የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ከኦሮሞዎች
ብቻ አይሆንም፡፡ እኔም ይህንን እንዳነሳ ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም የኦሮምኛ ቋንቋ ባልናገረውም የእኔም ቋንቋ ሃብቴ ነውና፡፡ ሃገሬ
ሁለትና በላይ ዋና ዋና ቋንቋዎች ቢኖራት የበለጠ ታተርፋለች እንጂ አትከስርምና፡፡
ሌላው መገንዘብ ያለብን አንድ ቋንቋ ዋና ሆነ ማለት የዚያ
ቋንቋ ፈጣሪ የሆነ ቡድን ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደልም፡፡ ቋንቋው ዋና በመሆኑ
የተለየ ተጽዕኖ ሊያሳድርም አይችልም፡፡ ሌላው መረዳት ያለብን ደግሞ ቋንቋዎች ወደ ዋና መግባቢያነት መምጣታቸው ለእንክብካቤ የተመቹ
እንዲሆኑና ሌሎቹ የመጥፋት አደጋ እንደተቃጣባቸው ተደርጎ ሊታሰብም አይችልም፡፡ በተግባር እንደምናየው እንደውም የመበወዝ /standardized የመሆን/
እድሉ ሰፊ የሚሆነው ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ
መስጠት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የአለም ቋንቋ የሆነውን እንግሊዘኛን ብንወስድ አሁን ያለውን የቋንቋውን ይዘት ስናይ 60% የሚሆነው
ቃል ከተውሶ የመጣ ነው፡፡ ከላቲን፣ ከጣሊያን፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ ወዘተ. የመጡ ቃላቶች የእንግሊዘኛ ቃልን በውዘውት አርባ በመቶ
የሚሆነው ብቻ ነው የኦርጂናሉ የእንግሊዞች እንግሊዘኛ ያለው፡፡ኣሁንም ገና እየተበወዘ ነው። ቴክኖሎጂ ሲያድግ፣ የኣለም ህዝቦች
ንቃት ሲጨምር እንግሊዘኛ እየተበወዘ ይሄዳል። በዚህ እንግሊዝ አልተከፋችም፡፡ ያላትን ቋንቋ ለአለም ህዝቦች መስዋዕት አድርጋ ቋንቋው
ሲያድግ የምትደሰት ነው የሚመስለን፡፡ ይህን ያመጣነው አንደኛ ቋንቋ አዳጊ መሆኑን እና በሌላ በኩል የመበወዝ እድሉ ሰፋ የሚለው
የብሄራዊ ዋና መግባቢያ የሆነው ቋንቋ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ዋናው ቡድኖች የሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ስምምነቱን ከልብ በመቀበሉ
ላይ ሲሆን ከዚያ በሁዋላ በዋና መግባቢያ ቋንቋ ላይ የሚደረገው ምርጫ ከፍ ባለ መረዳት ላይ ተመርኩዞ ስለሚሆን እንቅፋቶች አይገጥሙትም፡፡
አሁን ቡድኖች የኔም ቋንቋ ዋና መግባቢያ ይሁን የሚያስብላቸው
ነገር አንደኛ ፖለቲካው የብሄር በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ፈጣሪዎች የዚያን ቡድን ቋንቋና ባህል ለብቻቸው ስለተሸከሙ እና ፖለቲካው ራሱ
አእምሮአችንን ስለሚያሞስሰው /corrupted ስለሚያደርገው/ እንዲሁም አንድ ቋንቋ ዋና መግባቢያ በመሆኑ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ
ማህበረሰብ ይህን ተንተርሶ ሌሎች የስነ-ልቦናና የማቴሪያል ጥቅም ያገኛል የሚል ስሜት ስላለ ነው፡፡ እነዚህ ስሜቶች መጀመሪያውን
ወደ ስምምነቱ ስንመጣ የሚቀሉ ይሆናሉ።
ክፍል
ስምንት
ማጠቃለያ፣
የፖሊሲና የስትራተጂ ኣቅጣጫዎች
ይህ ንድፈ ሃሳብ
ዋናው ኣላማው በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ሲሆን ይህ ትራንስፎርሜሽን የማህበራዊ ፖለቲካችንን መሰረት ያስተካክላል
ወይም ይፈውሳል በሚል ልብ ነው። ዛሬ በሃገራችን ፍትህ ሲጎድል ስናይ ይህን ለመዋጋት ሮጠን የፖለቲካ ቤት የምንሰራበት መሰረት
ያስፈልገናል። ይህ መሰረት ኣንድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ማንነት ሲሆን ይህን ማህበራዊ ለውጥ ማስቀደሙ ጠቀሜታው ፖለቲካችንን ስለሚያስተካክለው ነው።
ጥቂት የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችን
ለመጠቆም ያህል ደሞ፣
1.
ሚዛናዊ የሆነ የባህል ውህደትን ማራመድ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አለ
የተባለው በሃይል የተደረገ የባህል ውህደት በሌሎች ዘንድ ሚዛኑን ያልጠበቀ ግን የከፋ አልነበረም የሚባለው ውህደት የታየው
20% ግድም በሚሆነው የከተማ ነዋሪው አካባቢ ነው፡፡ በየገጠሩ የሚኖረው ህብረተሰብ በባህል ደረጃ እምብዛም ለውህደት የተጋለጠ
አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ሚዛኑን የጠበቀ የባህል ውህደት ለማካሄድ ሰፊ እድል አላት፡፡ በመሆኑም
መንግስት ሚዛኑን የጠበቀ አቅጣጫ በማሳየትና በማበረታታት የባህል ፍስስቱን ባላንስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ቀላል ምሳሌዎችን እናንሳ፡፡
ለምሳሌ መዲናችን የሆነችውን አዲስ አበባን መልኳን ብናይ የብዙ ብሄሮች ርዕሰ ከተማ አያስመስላትም፡፡ አዲስ አበባ በነበርኩበት
ጊዜ አንድም ቀን የኮንሶዎች ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ በደቡብ አካባቢ የሚታወቀው የኩርኩፉ ምግብ ቤት አላየሁም፡፡ የሃመሮች ምግብ
ቤት፣ የቦረናዎች ምግብ ቤት ወዘተ አላየሁም፡፡ እነዚህ ቡድኖች የየራሳቸው ጣፋጭ የምግብ አሰራርና ዓይነት ቢኖራቸውም መዲናዋ ላይ
ገበያ ላይ አልወጣምና አዲስ አበባን እውነተኛ መልኳን እንዳታሳይ አድርጓታል፡፡ በሌላ በኩል ሰርግ የሚያደርጉ ድርጅቶች
(wedding halls) በውስጣቸው ብዙ የሰርግ ስርዓቶችን የሚያሳይ
ሜኒዩ (menu) ቢኖራቸው መልካም ነው፡፡ ተጋቢዎች ወደዚያ ሄደው ከሜኒዩው መርጠው በዚያ ስርዓት ቢጋቡ ደስ ይላል፡፡ ፍቅራችን፣
አክብሮታችንና፣ አንድነታችን፣ መቀባበላችን በዚህም ይገለጽ ነበር፡፡ በኣልባሳት በኩል፣ በሙዚቃ በኩል እንዲሁ የኢትዮጵያን ቡድኖች
የሚያሳዩ ቤቶች ሊታዩ ይገባል፡፡ ሚዛናዊ የባህል ውህደትን የሚያመጣው አንዱ የቡድኖችን ጥበብ በሚታይ ስፍራ በማውጣት ነው፡፡ ይህን
ማድረግ ይቻላል፡፡ይህን ስንል ምን ኣልባት ኣንዳንዶች ይህ ኣይነቱ ሂደት በፖሊሲ የሚሰራ ኣይሆንም መንግስት ኮንሶዎች እዚህ ጋር
ምግብ ቤት ክፈቱ፣ ሃመሮች እዚህ ቦታ ላይ መጠጥ ቤት ክፈቱ ኣይልም እንዲህ ኣይነት ስፔሲፊክ ጉዳይ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት የሚያመጣው
ነው ልንል እንችላለን። ግን ኣይደለም። መንግስት ከባቢየሆኑ ፖሊሲዎችን ማውጣት ይችላል። ከባቢዎች ሲኖሩ፣ ቡድኖች እውቅና ሲያገኙና
ስምምነቱ ሲገባቸው እነዚህ ጉዳዩች የመንግስትን ምቹ ፖሊሲዎች እየተከተሉ የሚከሰቱ ናቸው። የታቀደ ማህበራዊ ዲቨሎፕመንት ማምጣት
ይቻላል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ብሄር ያላቸው ኣገሮች በእቅድ በተደገፈ ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ ሲያልፉ ነው ሰላምና ልማታቸው
የሚጠነክረው። በሌላ በኩል ቋንቋዎችን ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ መንደፍ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአማራው አካባቢ የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማሪያ
አካዳሚዎች ቢኖሩ፣ በትግራይ የኮንሶዎችን ቋንቋ የሚያስተምሩ አካዳሚዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን እየተማሩ በዚያ ስራ
የመያዝ እድል ቢኖራቸው በዚያው የቋንቋ ሃብትን የመጠበቅ ሃላፊነት ሊወጡ ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ
የቱሪስት መስህብ ለማግትኘም ጭምር የባህል መንደር /cultural villages/ መመስረት፣ የባህል ተቋማትን በየቀበሌው ማቋቋም
ቡድኖች ሁሉ ነቃ ነቃ እንዲሉ በሃገራቸው ምስረታ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የባህል ልውውጥ ፕሮግራሞች
ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል በትምህርት ካሪኩለሞቻችን ውስጥም የተለያዩ ባህሎቻችንን እየሰገሰጉ ማስተማር ጠቃሚ የሆኑትን እየነቀሱ
እያወጡ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
2.
መልክአ ምድራዊ ተዋጽኦ /spatial diversity/
የሰፈራ
ፕሮግራሞች እንዲሁም የፌደራል ስርዓቱ ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረጉ ሳይሆን የህብረተሰቡን ተግባቦትም ያገናዘበ መሆን አለበት ብሎ
ይህ ንድፈ ሃሳብ ያምናል፡፡ አንዱ የአንድነት መገለጫ የመሬት አንድነት በመሆኑም ይህንን አንድነት የሚያሳይ መልክአ ምድራዊ አሰፋፈር
ያስፈልጋል፡፡
3.
በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቅርጽ መፍጠር
ሌላው
የታችኛውን ማህበራዊ ጉዳያችንን እያሻሻልን ሳለ ኣብረን ትኩረት ሰጥተን ልንፈታው የሚገባው ጉዳይ የፖለቲካ ኣወቃቀራችንን ነው።
የእኛ የኢትዮጵያዊያን ችግር የሚፈታው በዚህ በባህልና በቋንቋ አካባቢ ያለንን መዋቅር ስናሻሽል እና ፖለቲካችንን ከባህል ማንነት
አውጥተን ወደ ብሄራዊ ማንነት ስናሸጋግር ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅርጿን በ ኣንድ ብሄራዊ ማንነት ላይ በመስራት ማህበራዊ
ፖለቲካዋን ትራንስፎርም ልታደርግ ያስፈልጋታል። በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ውህደት ብሄራዊ እርቅን የሚያበረታታ፣ ለጋራ
በጋራ የምትሆን ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ /reinventing Ethiopia/ የሚረዳ ነው ብለን ኣምነን ነው፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
No comments:
Post a Comment