Friday, June 29, 2012

ከቤልጂየም የተማርነው

እኔ ደሞ አገር ያለ መንግስት የሚቆም አይመስለኝም ነበር አለኝ አንዱ ስለ ቤልጂየም የማእከላዊ መንግስት መዘጋት ስናወጋ:፡ የቤልጂየም ፖለቲከኞች ማእከላዊውን መንግስት ከ ጁን 2010 ጀምሮ በመቀመጫ ንትርክ ጥርቅም አርገው ዘግተውታል። አሁን ግን ቅንጅት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው መሰል። ቤልጂየም ደች ፈረንሳይኛ ና ጀርመንኛ ኦፊሺያል ቁዋንቁዋ ሲሆኑ በተፈጥሮዋ ብዙህ ናት።  
 ታዲያ የበልጂየም ፖሊቲከኞች ማእከላዊውን መንግስት ቢዘጉትም ቤልጂየሞች ወይ ፍንክች እንዴውም ምንም የጎደላቸው እስከማይመስሉ ደረሱ።  በዚህ የሃይል ክፍተት ጊዜ እንዴውም ህዝቡ ፍቅሩን ያሳየበት ታሪካዊ ጊዜ ሆኖ ታዬ:: መንግስታቸው ሲዘጋ የተለያዬ ቁዋንቁዋ ና ባህል ያላቸው በልጂየሞች አንድነታቸውን እና ፍቅራቸውን ከመቼውም አስበልጠው እያሳዩ ነው። አንድነታቸውን እና ፍቅራቸውን የተፈጠረው የሃይል ክፍተት እንደማይበግረው ባደባባይ አሳዩ። እንደው ለመሆኑ ቤልጊየሞችን ወደዚህ ከፍታ ያመጣቸው ምን ይሆን? በዚህ የሃይል ክፍተት ጊዜስ ቤልጂየምን እንደ መልህቅ ያቆማት ምንድርነው? ብለን መቼስ እንጠይቃለን። ታዲያ በዚህች በጣም አጭር ጽሁፍ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የመሳሰለኝን ለማቀበል ነበር የዛሬው ንሽጤ። በዚያው ክኛው ቤትም ጋር ለማዛመድ ልብ አለኝ።

የቤልጂየምን ክፍተት የሞሉ ጉዳዮች

1) ጠቃሚ ባህሉዋን የጠበቀች ሃገር ናት

መቼስ መንግስት ምን ጊዜም ቢሆን ቋሚ አይደለም:: ይመጣል ይሄዳል ደሞ ይመጣና ይሄዳል:: ፓርቲዎች ይሸነፋሉ ይሸነፋሉ። አዲስ አሳብ ሲመጣ አንዱ አመለካከት ሌላውን እየረታው ይነጉዳል። ልክ እንደ ጅረት ነው፡፤ በዚህ የለውጥ ሂደት ጊዜ አንዳንዴ ከ ፖለቲከኞች የተነሳ የሃይል ክፍተት (power vacuum)የሚባለው ነገር ሊከሰት ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ለሃገር ሰላም እና ልማት ጠቃሚ የሆኑ ባህሎችን መጠበቅ ለክፉ ቀን ጊዜ መላ ይሆናል:: የቤልጂየም መንግስት ሲዘጋ ንጉስ አልበርት ስልጣኑ የተወሰነ ክፍተቱን የሚሞላ (Caretaker) አቋቋሙ:: እኚህ ንጉስ ያቋቋሙት ይህ ቡድን ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት አደረገ:: በኛ ሃገር ለውጥ ሲመጣ በፍንዳታ መልክ ነው:: ሃይለስላሴ አቅማቸው እየደከመ ሲሄዽ እየበረታ በመጣው የለውጥ ፍላጎት ፈንጂ ተመቱ:: እንደው  ብልህነት ቢኖር ኖሮ ሰላ አድርጎ የፖለቲካ ስልጣኑን ከጃቸው ተቀብሎ የሳቸውን አስተዳደር ወደ ባህላዊ አስተዳደር የመቀየር ሂደት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ላዛሬው ችግር አንዳረግም ነበር። እርግጥ ነው ያ ትውልድ አዲስ ነገር ተገልጦለት ነበር። ድፍረቱ አገር ወዳድነቱ ቅርሳችን ነው። እንደው በንበል ገብያ ሆነን ስናወጋ ማለቴ ነው በዚያን ጊዜ አዲሱ አስራር አዲሱ ርእዮት ሲገለጥ ሽማግሌውን ወደ ጉዋሮ ወስዶ አፍኖ ከመግደል አስተዳደሩን ወደ ባህር ከመወርወር ቀስ ብሎ የፖለቲካ ስልጣኑን ዘመንኛ አርጎና አሰራሩን ቀይሮ አሮጌውን ስርአት ደሞ ወደ ባህላዊ አስተዳደር በመቀየር አዲሱን ራእይ ማስረጽ ይቻል ነበር። ሽማግለው በራሱ በግዜር ጊዜ ቢሄዱ አሳልፈው ለልጃቸው ቢሰጡ ችግር አልነበረውም። ወድጃቸው ወይ ደግፊያቸው አይደለም። አሮጌውን ስርአት ከነ ነፍሱ ወደ ሙዚየም አስገብተን ብንሮጥ የትውልድ ክፍተትን እየዘጋን የጨቁዋኝ እና የተጨቁዋኝ ትግል ክብ ውስጥ አንገባም ነበር ይሆናል። ጨቁዋኙ እንደገና ተጨቁዋኝ ሳይሆን ተጨቁዋኙ ቡድን እንደገና ጨቁዋኝ ሳይሆን ሁለቱም ነጻ የሚሆኑበት መሰረት ቢጣል ኖሮ አሁን ላለንበት አሳፋሪ ሁኔታ አንደርስም ነበር መሰለኝ። ለውጡ በፍንዳታ መልክ ሲመጣ ብዙ ሰው ጨረሰ። አብዮቱ ሲፈንዳ በድንጋጤ ብዙ ጠቃሚ እሴቶችን ሁሉ ከጃችን አስረገፈን። የተደራጁት የኛው ወንድሞች ወታደሮቹ አገር መጠበቅን የመሰለ ትልቅ ሃላፊነት ትተው በህዝብ ልብ የመጣወን የለውጥ ግፊት እኛ ነን የተረዳነው እኛ እንመራዋለን ብለው ተነሱ። ወዲያውም ክምስራቅ የተነሳ አውሌ ነፋስ አገኘን። ይህ የግራ ክንፍ የሚባለው ነገር ያጣወላቸው አገሮች መቅኖም የላቸው። የመጣው አብዮት የበፊቱን ጨቁዋኞች አደገኛ ተጨቁዋኝ አድርጎ በከፍተኛ ጥላቻ ላይ ባንዲራወን አውለበለበ። አጥፊና ጠፊ ሆነ ፖለተካው። አይጥና ድመት።

ትዝ ይለኛል ባደኩባት ትንሽ ከተማ ውስጥ ለልጆች የሚሆን መጫወቻ ማግኘት አይቻልም ነበር።
ቆርኪ ደሞ እንዲሁ የወደቀ ፖስተር ካገኘን ትልቅ ነገራችን ነበር። አንዴ ታዲያ ወደ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ሄድኩ መጫወቻ ለመለቃቀም። በዚያም አንድ የተባረኩ የጽ/ቤቱ ሰራተኛ ምን ትፈልጋለህ አሉኝ? ያባቴ ጉዋደኛ ስለሆኑ ያውቁኛል። መጫወቻ አልኩዋቸው። ወደ ማእከሉ ገቡና ያረጀ የታይፕ ሪቫን፡ የወዳደቁ ክላሰሮች እና አንድ ትልቅ ፖስተር ሰጡኝ። በደስታ እየዘለልኩ ወደ ቤቴ አመራሁ ። ቤቴ ስደርስ እናቴ በትልቁ ፖስተር ላይ አይንዋ አረፈ ። ለግድግዳችን ይሆናል ብላ ከኔ ወስዳ በ ሙቅ ብጤ ለጠፈችው። ፖስተሩ የሚያሳየው አንድ ጡንቻው የፈረጠመ ሰውየ እንደ ኦክቶፐስ(አሁን ነው አክቶፐስ መምሰሉ የገባኝ) የመሰለ ጭንቅላቱ ብዙ ስራስር ያለውን ፍጡር በድንጋይ መራጃ ሊበረግደው እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። ከተለጠፈ በሁዋላ ከገጠር የሚመጡ ዘመዶቻችን ጥያቄ ያነሱ ጀመር ይሄ ፍጡር ምንድነው? ባለ መራጃው ማነው ይሄ ልዩ ፍጡርስ ምን ይሆን? የብዙዎቹ ጥያቄ ነበር። ለነገሩ አባቴም አልገባውም። ብቻ ከሰር የተጻፈውን ስላነበበውኢምፔሪያሊዝም ነው ጋሼ እንትና እያለ ቁጭ ይላል። አንድ ቀን ታዲያ ሁለት እንግዶች ክጭቃ አሳብደን የሰራናት መደብ ላይ ተሰይመው ቀና ብለው እያዩ ስለ ስእሉ ይወያዩ ነበር። አንዱ ባለመራጃው እንሆ ቅዱስ ጊዎርግስ በቁጣ በዲያቢሎስ ላይ ተነስቶ ነው አሉ። ሌላኛው ሰውዬ ግን አይ ተወኝንስ ያጥፊና የጠፊነት ምስል ነው አሉ። ምን ለማለት ነበር ይህን ያመጣሁት መጥቶ የነበረው ለውጥ በጥላቻ ላይ በመመስረቱ ና ዘለግ ብሎ ካህዝቡ መረዳት ጋር ባለመሄዱ የበለጠ ኪሳራ አመጣ። ጨቁዋኝ የተባለውን ወገን እንደ ውጭ ጠላት በመቁጠር ሁለት ቤት ያለው አንዱን እንዲቀማ ተደረገና አንዳንድ ክፍል ቤት ተከፋፍለን ቁጭ አልን። መሬት ላራሹን የመሰለ ትልቅ ጥያቄ ብልሃት በጎደለው ለመመለስ በመሞከሩ መሬታችን ተበጣጠሰ ባለቤትነቱንም ራሱ መንግስት ወስዶት አረፈ። ዘጠኝ ድሃ ቤተሰብ ያለው አንድ ሃብታም ከርሞ አስር ይሆናሉ እያልን የምናዜመውን የገዛ ብሂላችንን በተግባር አሳይተን ቁጭ አልን። ያ የኮሚኒዝም ጊዜ የጎዳን ከምንም በላይ ማህበራዊ ሃብታችንን መጉዳቱ ነው። የተከበሩ የእምነት መሪዎችን ከአብዮቱ እንዲያጠቅሱ እየተደረጉ ቀልባቸውን ማጣት ጀመሩ። ጥሩ ጥሩ እሴቶቻችንን ሁሉ በጎታች ና ባድሃሪ ስም ተደመሰሱ። መጣል የሌለብንን እየጣልን ማንሳት የሌለብንን እያነሳን ሮጥን።

ደሞ እነዚህ መጡ:: የፈረሰውን ያዘመመውን ማህበራዊ ሃብታችንን እና ኢኮኖሚያችንን ይጠግናሉ የሚል ተስፋ በየዋሆች ዘንድ ተሰማ:: ይሁን እንጂ እነሱም እንዲሁ በፍንዳታ ጀመሩ ለውጡ ስር ነቀል ነው ተብሎ የደርግ መሰረተ ትምህርት ዘመቻ ሳይቀር ችላ ተባለ:: አንዴ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንዴ ሶሻሊስት አንዴ ካፒታሊስት እያሉ ርእዮት እንደሌላቸውም አስመሰከሩ::ገቡና አዲሳባ ሲያበቁ በስልጣን ለመቆየት የሚያስችላቸውን ዘዴ ሲመርጡ እነዚህን የሃይማኖትና የባህል መሪዎችን ካብዮታዊ ዴሞክራሲም ይበሉት ከምናምን እንዲያጠቅሱ ማድረግ ህዝቡን ለመያዝ የሚይስችል አንድ መንገድ መስሎ ታያቸው  ይሁን እንጂ ህዝቡ የመጨረሻውን እነሱን ሲጠላ ያጠቀሱትን ሁሉ ከሚዛን አቀለላቸው:: ክቡር ዶክተር ብርሃኑ እንዳለው ሽምግልና ሳይቀር ተዋረደ:: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሊቃነ ጳጳሱ በ ድንጋይ ተሞከሩ:: እንደው የሆነ የሃይል ክፍተት ቢመጣ ውጉዝ ከመ አርዮስ አንተም ተው አንተም ተው ብለው ብጥብጥ ለማስቆም ሃይል የነበራቸው ሃይማኖታዊ መሪ እንዲህ እንዲህ ተሞከሩ:: በ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ተውግሮ የሚሞተው ከባድ ሃጢያት የሰራ አመንዝራ ነው። አመንዝራ ማለት ጻታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጣኦት ማምለክ ወይም ሃይማኖትን ማፍረስ ማለት ነው። ጳጳሱ እጃቸው ፖለቲካ ወስጥ ገብቱዋል መባላቸው ብቻ ሳይሆን በጋዜጦች ላይ ሽጉጥ ተሸልመው የታጋይነት ማእረግ ደፉ። ከባድ ታሪካዊ ነገር ተፈጠረ።

በአኦሮሚያ በኩል የነበሩ ለአለም ዴሞክራሲን ለማስተማር የበቁ ተቋሞች ሃይላቸው ተገፈፈ። የእድር ዳኞች የቤተ ዘመድ ሰብሳቢዎች ሳይቀሩ ፎርም እየሞሉ በ ፖሊቲካ ተጠመቁ።ይህ ሁኔታም መንግስት በተናወጠ ጊዜ መተማመኛ የለንም ብለን እንድንተክዝ አደረገን:: እነዚህ ተቁዋማት ለህዝቡ ላይኑ ማረፊያም እንዳይሆኑ ተደረጉ። ቤልጂጎች ከተው ሲንከባከቡት የነበረው ባህላዊ አስተዳደራቸውን በችግር ጊዜ መዥረጥ አረጉት:: ሌላ የውጭ ወገን ሳያስፈልጋቸው ኬር ቴከር አቋቋሙ::

2) ጠንካራና ነጻ ተቋማት መኖራቸው

 በቤልጂየም መንግስትና ፓርቲ ይለያያሉ:: በተለይም በተፈጥሮአቸው ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ መሆን ያለባቸው እንደ ፍርድ ቤት ባንክ ሲቭል ሰርቪስ ፖሊስ ወታደር የመሳሰሉት እዚያ አገር ነጻ ናቸው:: በፖለቲከኞቹ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መንግስት ሲዘጋ ፖሊቲከኞቹ ስላልተናደዱ አሳባቸውን ለመፈጸም ስላልተቆጡ አይደለም:: ነገር ግን ይህ ቁጣና ንዴት ወደ ከፋ ሊለውጡት አይችሉም:: ህግ አይፈራቸውምና:: እነሱ ግን ከህግ የበታች እንደሆኑ ስለሚያውቁ ምን ቁጣ ቢያሳብዳቸው መስመሩዋን አያልፉም:: በመሆኑም ፖለቲከኞቹ ባለመግባባት ማእከላዊ መንግስቱን ቢዘጉትም ፖሊሱ ከማናቸውም ሳይወግን ወታደሩ ሳይወግን ፍርድ ቤቱ ሳይወግን ቀጥ ብለው ስራቸውን ቀጠሉ:: ወታደሩ መሃላውን ሰብሮ ይህችን ክፍተት ተጠቅሞ ግርግር በመፍጠር ስልጣን ለመያዝ ጨርሶ አልዳዳውም::

ወደኛው ቤት ስንመለስ የኢትዮጵያን ፍርድ ቤት ከፓርቲው ውጭ ምን እንደሚመስል ለማየት ይከብዳል::ደሞ በህዝብ ዘንድ እንዳሁኑ ጊዜ ባገራችን ፍርድ ቤት የቀለለበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም:: ባለፈው ጊዜ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ሰው ገለሃል ተብሎ ሲታሰር ቴዎድሮስ እኔ ከደሙ ነጻ ነኝ ሲል የህዝብ ጠበቃው ደሞ ገለሃል ይለዋል። ፍድ ቤቱም የፍትሁን ሂደት አየሁት ቴወድሮስ ጥፋተኛ ነው ብሎ ፈረደበት:: የሚገርመው ታዲያ ህዝቡ ቴዎድሮስ ይሁን ትክክሉ የፍርዱ ሂደት ይሁን ትክክሉ በአይኑ አላየም ይሁን እንጂ ያ ሁሉ ህዝብ ፍርድ ቤቱን ሳይሆን ቴዎድሮስን ነበር የሚያምነው:: አንድ ግለሰብና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቆመው ሲሟገቱ ገለሃል አልገደልኩም ሲሉ ህዝቡ ግለሰቡን ካመነ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ባይፈጠር ይሻለው ነበር:: እንዴት ይህን ያህል ከግለሰብ ተወዳድሮ እምነት ያጣል? ይህ ፍርድ ቤት በቁሙ ስለሞተ በሃገራችን ለሆነ ክፍተት አያግዘንም እንዴውም አንዱ የመጬቆኛ መሳሪያ ሆኑዋል:: ባንኮች ፖሊስ ወታደር ነጻ አይደሉም ማለት ለህዝብ አልወገኑም ማለት ነው ስለዚህ ከሚመጣ ክፍተት አገር ለመታደግ የሚችሉ አይነት አይደሉም::ቤልጂየሞች ግን የጸዳ ፍርድ ቤት ስላላቸው ፖለቲከኞች ባይኖሩም ችግር የለውም።


 3) ህዝቡ አንድነቱን ማፍቀሩ

 መንግስት ከተዘጋ በሁዋላ ቤልጂየሞች ከሁሉም ቋንቋ ተናጋሪዎች እየሆኑ ያንድነት ድግስ ሲበሉ ነበር፡: ይህ ከምንም በላይ ነው:: በኛ ሃገር የሆነ የሃይል ባዶነት ቢፈጠር አለን ብየ እንዳንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የምኮራው በዚህ ብቻ ነው:: ኢህአዴግ በጎሳና በቋንቋ ከፋፍየዋለሁ ለረጅም ጊዜም ለመግዛት ይመቸኛል ሲል ህዝቡ ፍቅሩን በልቦናው ጨብጦ በ1997 ምርጫ ጊዜ ያሳየው መተሳሰብና አንድነት የሚመጣውን ማንኛውንም ለውጥ ለመቆጣጠር የሚችል ብቸኛ ሃብታችንና ሃይላችን ነው:: ይህ ሃብት ከሁሉ ይበልጣል:: ከላይ አጣናቸው ብዬ ላጉረመረምኩባቸው ብሶቶች ሁሉ ካሳችን ይሄ ነው እና መጠበቅ አለብን::

እነዚህ የረከሱብን ያልናቸው የሽምግልና ባህላችን የእምነት መሪዎች ተከባሪነት ባህላችን ሁሉ
በህዝቡ አብራክ ውስጥ አሉ። ዋናው ህዝቡ በልቦናው ፍቅርን እና አንድነቱን መጠበቁ ሲሆን
በጊዜው ጥሩ ጥሩ ሽማግሌዎች ጥሩ ጥሩ መሪዎች ቅዱሳን የሃይማኖት መሪዎች ተሰሚነት ያላቸው
ግለሰቦች ነጻ ፍርድ ቤት ነጻ ወታደር ወዘተ. ይወለዳሉ።

አንዳንዴ ግን ቅር የሚያሰኘን ነገር ደሞ አለ:: ህወሃት አዋጭ ነው ብሎ ካመነበት አንዱ ይሄው በጎሳ በጎሳ ከፋፍሎ ጥላቻን በመዝራት በስልጣን መቆየት ነው:: ታዲያ ይህ ተልእኮው በተወሰነ ደረጃ ውጤት ያስመዘገበለት በዲያስፖራው ዘንድ ነው::በዚህም የተደሰቱ ይመስላል:: እንዴት ዲያስፖራው ለዚህ ከፋፋይ ተግባር እንደተመቸ እግዜር ይወቅ:: ትግሬው አማራው ኦሮሞው ካገር ሲወጣና ሲማር የበለጠ ሊቀራረብ ህብረቱን በማሳየት ክፍተት እንዳይኖር ሊያደርግ ሲጠበቅበት ሳያውቀው የወያኔ ሰለባ የሆነ ይመስላል:: መከፋፈሉ ካገር ቤት ይልቅ በውጭ ባሉት ኢትዮጵያዊያን ይበረታል። በመከፋፈል የሚያተርፈው ገዢው መንግስት ብቻ ነው::በመሆኑም ሳናውቀ ለግዢው መንግስት ስልጣን ማራዘሚያ እየሆንን ይመስላል።

ዲያስፖራው የበለጠ ፍቅርን ማሳየት አገራዊ አደራው ነው:: እኛ ኢትዮጵያዊያን ህብረት ያስፈልገናል ህብረት ህብረት ህብረት. . .ስንል ዋናው መነሻችን ወያኔን ለመጣል አይደለም ከዚያም በሁዋላ የጋራ መንግስት ለመመስረት እንዲያስችለንም አይደለም ዋናው የህብረታችን መሰረት ተፈጥሮአችን ራሱ ህብረት በመሆኑ ነው:: እኛ ኢትዮጵያዊያን ብዙህ ነን በተፈጥሮአችን ። ይሄ ተፈጥሮአችን ነው የህብረታችን ዋናው መሰረቱ:: ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዝንጉርጉርነቱን አይስትም ይላልና መጽሃፉ::

                       
        ቸር ይግጠመን
          
ገለታው ዘለቀ

No comments:

Post a Comment

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...